የስፔን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሆዜ ማኑኤል አልባሬዝ ይህን የተናገሩት፤ ዕሑድ እለት ማድሪድ ባስተናገደችው የ20 የአውሮፓ የውጭ ጉዳይ ተወካዮችን፣ ሙስሊም ሀገሮችን እንዲሁም ብራዚልን ባሳተፈ ጉባዔ ላይ ነው፡፡ ጉባዔው የተሰናዳው በጋዛ የሚፈጸመውን ጥቃት እንዴት ማስቆም ይቻላል በሚለው ላይ ለመምከር ነው፡፡ እግረ መንገድ ግጭቱን በዘላቂነት ለመፍታት የሁለት ሀገረ መንግሥት ምሥረታ አስፈላጊነት ተነስቷል፡፡
አልባሬዝ በውይይቱ ላይ ለፍልስጤም ሀገረ መንግሥት ዕውቅና በመስጠት ሁለት ሀገር ምሥረታን ዕውን ማድረግ ይገባል ሲሉ ወትውተዋል፡፡ ሁለት ሀገረ መንግሥት መመሥረት ካልተቻለ “ታድያ አማራጩ ምንድን ነው?” ያሉት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ “ሁሉንም ፍልስጤማውያን መፍጀት ወይንስ ወደ የት እንደሆነ ባላውቅም [ምናልባት] ወደ ጨረቃ መሸኘት ነው?” ሲሉ በግራ መጋባት ጥያቄ ሰንዝረዋል፡፡
በጋዛ የሚሰማውን ሰቆቃ ለመግለጽ የሚቻልበት ቃል እንደሌለ የተናገሩት አልባሬዝ፤ “ሰቆቃውን የሚገልጽ ቃል የለም ማለት ግን የሚፈጸመውን እንዳላየ በዝምታ ማለፍ አለብን ማለት አይደለም” ብለዋል፡፡
አልባሬዝ ሀገራቸው በቀጣይም ቢሆን የጋዛ ጥቃት እንዲቆም የምታደርገውን ግፊት እንደምትቀጥል በመግለጽ፤ ይህ አውሮፓ ኅብረት ከእስራኤል ጋር የሚኖረውን የንግድ ውል ማቋረጥን የሚያካትት እንደሚሆን ጥቆማ ሰጥተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በጥቃቱ ላይ እጃቸው አለበት የሚባሉ ግለሰቦች ላይ ማዕቀብ መጣልም እንደ አማራጭ እንደሚቀመጥ ገልጸዋል፡፡
አክለውም ስፔን በቀጣይ ሰኔ ወር የሚካሄደውን የተባበሩት መንግሥታት ስብሰባ “የፍልስጤም ሀገረ መንግሥት ዕውቅና እንዲሰጠው ለማድረግ ንቅናቄ ለመፍጠር ምክረ ሐሳብ ታቀርባለች” ብለዋል፡፡ “ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ ደግሞ ፍልስጤም በተባበሩት መንግሥታት ውስጥ የተሟላ መብት ያለው መንግሥት ሆና ሌላ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ማካሄድ እንችላለን” ብለዋል።
በቀጣይ ወር የሚካሔደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስብሰባ በሳዑዲ ዐረቢያ እና ፈረንሣይ የተዘጋጀ ነው፡፡ ፈረንሣይ በጉባዔው ላይ ለፍልስጤም ሀገረ መንግሥት ዕውቅና እንደምትሰጥ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከጥቂት ሣምንታት በፊት ተናግረዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












