Homeዜናና ወቅታዊዜናበበደሌ ከተማ የሚገኘው የቡልቲ ኦዳ መስጅድ በእሳት ቃጠሎ ወደመ

በበደሌ ከተማ የሚገኘው የቡልቲ ኦዳ መስጅድ በእሳት ቃጠሎ ወደመ

በኦሮሚያ ክልል ቡኖ በደሌ ዞን በደሌ ከተማ ውስጥ በተለይ በአካባቢው የሚገኘው በመንግሥት ስር የሚተዳደር አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የሚጠቀሙበት የቡልቲ ኦዳ መስጅድ በእሳት ቃጠሎ መውደሙን “ሚንበር ቲቪ” ከኦሮሚያ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ከፍተኛ ኃላፊ ሰምቷል፡፡ የመስጅዱን ውድመት ተከትሎ በዛሬው እለት የአካባቢው ሙስሊም ማኅበረሰብ አጥፊዎች ለሕግ እንዲቀርቡ በሠልፍ ጠይቋል፡፡

የኦሮሚያ እስልምና ጉዳዮች የወጣቶች፣ የሴቶች እና አደረጃጀት ኃላፊ ኡስታዝ ሹዓይብ ሸምሱ ለ“ሚንበር ቲቪ” እንደተናገሩት፤ የመስጅዱ ቃጠሎው የተከሰተው እሑድ አመሻሽ ከ11 ሰዓት በኋላ ነው፡፡ በእሳት ቃጠሎ ሳቢያ መስጅዱ ሙሉ ለሙሉ ውድመት ደርሶበታል፡፡ ይሁን እንጂ የቃጠሎው መንስዔ እስካሁን ድረስ አለመታወቁ ተገልጿል፡፡

የቡልቲ ኦዳ መስጅድ በአካባቢው የሚገኘው የመንግሥት አዳሪ ትምህርት ቤት ሙስሊም ተማሪዎች ግቢ ውስጥ ሰላት እንዳይሰግዱ ክልከላ ተጥሎባቸው ከአካባቢው ሙስሊም ማኅበረሰብ በተገኘ መሬት ላይ እንደተገነባ ታውቋል፡፡ በትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ ሰላት እንዳይሰግዱ ክልከላ በተጣለባቸው ተማሪዎች ላይ ከፍተኛ ጫና ከማድረግ ባሻገር የተባረሩ ተማሪዎች እንደነበሩም ተገልጿል፡፡ በጫና ውስጥ ያለፉት ተማሪዎች ግንባታውን ያካሄዱት ቲኬቶችን ከመሸጥ አንስቶ የተለያዩ ገንዘብ ማግኛ መንገዶችን በመጠቀም እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፣ ሊጠናቀቅ ሲቃረብ በእሳት እንዲወድም ተደርጓል፡፡

መስጅዱ በእሳት መውደሙን ተከትሎ የኦሮሚያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት፤ በአካባቢው ከሚገኘው የምክር ቤቱ መዋቅር ጋር በመነጋገር ጉዳዩን ለሕግ አካላት እንዲመራ ማድረጉን ኡስታዝ ሹዓይብ ሸምሱ ጠቁመዋል፡፡ ምክር ቤቱም የመንግሥት ፀጥታ አካላትን ጨምሮ ጉዳዩን በማሳወቅ ክትትል እያደረገ ነው ብለዋል፡፡

መስጂዱ በእሳት ከወደመ በኋላ ዛሬ ሰኞ ግንቦት 18/2017 ረፋድ ላይ የአካባቢው ሙስሊም ማኅበረሰብ መንግሥት የመስጅዱን የእሳት ቃጠሎ ምክንያት በማጣራት አጥፊዎችን ለሕግ እንዲያቀርብ ጠይቋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular