የፍልስጤሙ ሐማስ በአሜሪካ የቀረበውን የተኩስ አቁም ስምምነት መቀበሉን አልጀዚራ ምንጮች ነግረውኛል ብሎ ዘግቧል፡፡ እንደ ዘገባው ከሆነ፤ የሀገሪቱ የመካከለኛው ምሥራቅ ልዩ ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ ከሐማስ መሪዎች ጋር በኳታር ዶሐ ተገናኝተው በቀረበው ሰነድ ላይ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡
ስምምነት ተደርሶበታል በተባለው ስምምነት፤ በጋዛ በሁለት ዙር የሚተገበር ለ60 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ሲደረግ፣ በእስራኤል ማጎሪያ ቤቶች የሚገኙ በርካታ ፍልስጤማዊያን እንዲለቀቁ ይደረጋል፡፡ በተጨማሪም ስምምነቱ ከተፈረመበት የመጀመሪያ ቀን አንስቶ “ያለ ቅድመ ሁኔታ” ወደ ጋዛ የረድኤት አቅርቦት ክፍት ይደረጋል፡፡ በምትኩ ሐማስ 10 ምርኮኞችን የሚለቅ ይሆናል፡፡ እነዚህ ምርኮኞች በሕይወት ያሉትንም ሟቾችንም ያጠቃልላል፡፡
ሐማስ በአሜሪካ በቀረበ የተኩስ አቁም ላይ ተስማምቷል መባሉን እንደ አልጀዚራ ሁሉ ሬውተርስ የዜና ወኪልም አንድ ሥማቸውን ያልጠቀሳቸውን የፍልስጤም ምንጭ ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ በሬውተርስ ዘገባ መሠረት የቀረበው ውል በአሜሪካ የመካከለኛው ምሥራቅ ልዩ ልዑክ የቀረበ ቢሆንም ባለሥልጣኑ ‘ያቀረብነው ሰነድ ሌላ በሚል’ ማስተባበያ ሰጥተውበታል ተብሏል፡፡

በተመሳሳይ የአልጀዚራ ምንጮች ሐማስ ከአሜሪካ ከስምምነት ላይ ደርሷል ቢሉም፤ ለስቲቭ ዊትኮፍ ቅርበት ያላቸው ሌላ ምንጭ ውድቅ አድርገውታል፡፡ ሐማስ በበኩሉ በወጣው መረጃ ላይ ይፋዊ መግለጫ አልሰጠበትም፡፡
የጋዛን ተኩስ አቁም በተመለከተ እርስ በእርሳቸው የሚጣረሱ መረጃዎች እየወጡ የሚገኙት የእስራኤል ወታደሮች በከተማዋ የሚሰነዝሩትን ጥቃት አጠናክረው በቀጠሉበት ወቅት ነው፡፡ የእስራኤል ባለሥልጣናት በጋዛ ከሚሰነዝሩት የቦምብ ጥቃት በተጨማሪ የረድኤት መተላለፊያዎችን በመዝጋት መሠረታዊ አቅርቦት እንዳደርስ ማድረጋቸውን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡ በቀጠለው ጥቃት ሰኞ እለት ብቻ ቢያንስ 81 ንጹሐን መገደላቸውን ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡
ሐማስ ከእስራኤል ጋር የሚያደርገውን ድርድር በተመለከተ ባለፈው ሣምንት ዘገባ ያወጣው የአሜሪካው መገናኛ ብዙኃን ሲኤንንኤን፤ በድርድሩ ሒደት ፕሬዝዳንት ትራምፕ በእስራኤል አካሔድ ደስተኛ አለመሆናቸውን የዲፕሎማቲክ ምንጮችን ነግረውኛል ብሏል፡፡ አሜሪካ በዶሐ ከሐማስ መሪዎች ጋር ለድርድር የተቀመጠችው በትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የዐረብ አሜሪካዊያውያንን ድምጽ ለመቀራመት ሲያስተባብሩላቸው የነበሩትን የፍልስጤም የዘር ግንድ ያላቸውን ቢሻራ ባህባህ የተባሉ ግለሰብን ነው፡፡ በዚህ ሒደት ቅዳሜ እለት ሐማስ እና እስራኤል ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ድርድር ማካሄዳቸው በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
ከዚህ ቀደም በሐማስ እና እስራኤል መካከል የሚካሄደው ድርድር የሚመራው በኳታር እና ግብጽ ባለሥልጣናት ፊት አውራሪነት እንደነበር ዘገባው አስታውሷል፡፡ ዘገባው ቢሻራ ባህባህ የተባሉት ግለሰብ የትራምፕን አስተዳደር በመወከል ከሐማስ መሪዎች ጋር ቢደራደሩም በሂደቱ ፍሬያማ ይሆናሉ የሚለው ላይ አንዳንዶች ጥርጣሬ እንዳላቸው አመላክቷል፡፡
የእስራኤል ወታደሮች ባለፈው አንድ ዓመት ከመንፈቅ ጊዜ ውስት በሰነዘሩት ጥቃት ቢያንስ 53 ሺሕ ፍልስጤማውንን መግደላቸውን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












