Homeዜናና ወቅታዊዜናየመጅሊስ ምርጫ “አንድነትን በሚያጠናክር መንገድ እንዲጠናቀቅ” ሁሉም አካላት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ...

የመጅሊስ ምርጫ “አንድነትን በሚያጠናክር መንገድ እንዲጠናቀቅ” ሁሉም አካላት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ

በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ስር የተዋቀረው የ2017 ምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ ጽሕፈት ቤት፤ በቀጣይ የሚካሄደው የመጅሊስ ምርጫ “አንድነትን በሚያጠናክር መንገድ እንዲጠናቀቅ” ሁሉም አካላት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ ያቀረበው በዛሬው እለት ነው፡፡

ይህ ጥሪ የቀረበው በሀገር አቀፍ ደረጃ ለምርጫ አስፈጻሚዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የምዝገባ መርሐ ግብር ማስጀመሪያ በአዲስ አበባ ከተማ ሚሊንየም አዳራሽ በተካሄደበት ወቅት ነው፡፡ ዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 19/2017 እየተካሄደ በሚገኘው መርሐ ግብር ላይ ከሁሉም ክልሎች እንዲሁም ከአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የተወከሉ ምርጫ አስፈጻሚዎች እንዲሁም “ሚንበር ቲቪ”ን ጨምሮ ለምርጫው ዘገባ ሽፋን የሚሰጡ መገናኛ ብዙኃን የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

በታላቁ አንዋር መስጂድ ኢማም ሐጂ ጣሃ ሙሐመድ ሐሩን ቁርኣን በተከፈተው መድረክ፤ በጠቅላይ ምክር ቤቱ ስር የተዋቀረው የምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ ጽሕፈት ቤት ሰብሳቢ ዶክተር ዓብዱልዓዚዝ ኢብራሂም ንግግር አድርገዋል፡፡ ሰብሳቢው በንግግራቸው ጥር 24/2017 ጠቅላይ ምክር ቤቱ ባደረገው አስቸኳይ ጉባኤ እርሳቸው የሚመሩት ዘጠኝ አባላት የምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ ከተቋቋመ በኋላ ተሠርተዋል ያሏቸውን ሥራዎች እንዲሁም ቀጣይ ተግባራት ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በቀጣይ ምርጫውን ለማካሄድ በሀገር አቀፍ በአራት ክላስተር መደራጀቱንም ሰብሳቢው ገልጸዋል፡፡ በዛሬው መርሐ ግብር ላይ የክልል ተወካዮች የምርጫ ሰነድ ርክክብ ያደረጉ ሲሆን፣ ምርጫውን ለሚዘግቡ መገናኛ ብዙኃን የዘገባ ፍቃድ ተሰጥቷል፡፡ በመድረኩ ላይ የምርጫው የጊዜ ሰሌዳ ይፋ አልተደረገም፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በጥር ወር ይፋ ባደረገው የምርጫ አፈጻጸም መመሪያ መሠረት፤ ቀጣዩ የጠቅላይ ምክር ቤቱ ምርጫ የሚካሄደው በሁሉም ክልል እና የከተማ አስተዳደሮች ነው፡፡ ምርጫውን ለማከናወን የምርጫ አስፈጻሚ አካላት የሚቋቋሙት በፌዴራል፣ በክልል/የከተማ አስተዳደር፣ የዞን/ልዩ ዞን/ ክፍለ ከተማ/ ዲያስፖራ ቅርንጫፍ፣ የወረዳ/ ልዩ ወረዳ/ የቀበሌ እንዲሁም የመስጂድ በሚል አደረጃጀት እንደሆነ ይገልጻል፡፡ በዚህም በፌዴራል ደረጃ ዘጠኝ፣ ለክልል/ከተማ አስተደደር ሰባት፣ ለዞን/ክፍለ ከተማ እና ዲያስፖራ አምስት እንዲሁም ለቀበሌና መስጂድ ደግሞ ሦስት ነው፡፡

ምርጫውን በተመለከተ የዑለማ ምክር ቤት ግንቦት 7/2017 በሰጠው መግለጫ፤ “በኢስላም መሪን መምረጥ” ተቀባይነት ያለው መሆኑ በተለያዩ የሸሪዓ ማስረጃዎች የተረጋገጠ መሆኑን በመግለጽ፤ የዑለማ ኮሚቴው፤ ምርጫ “ከተፈቀዱ ማኅበራዊ ጉዳዮችና ውሎች ውስጥ የሚመደብ” መሆኑንም አስታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ ተመራጮች “የምረጡኝ ቅስቀሳ” ማድረግ እንደሌለባቸው ያስታወሰው ኮሚቴው፤ “እንዲያውም ለሥልጣን መጓጓት አደገኛ መሆኑን በሰፊው ማስገንዘብ ይገባል” ብሏል፡፡

የጠቅላይ ምክር ቤቱ የወቅቱ ኃላፊዎች ወደ ሥልጣን የወጡት በ2014 እንደነበር ይታወቃል፡፡ የምክር ቤቱ የዑለማ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ ለአመራሮቹ የሰጠው ሦስት ዓመት የሥልጣን ጊዜ በሐምሌ ወር ይጠናቀቃል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular