Homeዜናና ወቅታዊዜናበዓለም ጤና ድርጅት የጄኔቫ ዋና ጽ/ቤት የፍልስጤም ሰንደቅ ዓላማ እንዲውለበለብ ውሳኔ ተላለፈ

በዓለም ጤና ድርጅት የጄኔቫ ዋና ጽ/ቤት የፍልስጤም ሰንደቅ ዓላማ እንዲውለበለብ ውሳኔ ተላለፈ

የዓለም ጤና ድርጅት የፍልስጤም ሰንደቅ ዓላማ በጄኔቫ ዋና ጽ/ቤት እንዲውለበለብ የሚደግፈውን የውሳኔ ሐሳብ በአብላጫ ድምጽ ያጸደቀው ማክሰኞ እለት ባካሔደው ስብሰባ ነው፡፡

የውሳኔ ሐሳቡ ከአባል ሀገሮች መካከል 95 ድጋፍ ሲያገኝ፣ እስራኤልን ጨምሮ አራት ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡ የድጋፍ ድምጽ ከሰጡት ውስጥ በቀጣይ ሰኔ ወር ለፍልስጤም ሀገረ መንግሥት ዕውቅና እንደምትሰጥ ያሳወቀችው ፈረንሣይ እና ጃፓን ይገኙበታል፡፡ ከእስራኤል ጋር የወገኑት ደግሞ ሐንጋሪ፣ ቼክ ሪፐብሊክ እና ጀርመን ናቸው፡፡ 27 ሀገሮች ድምጽ ተዐቅቦ በሰጡበት የውሳኔ ሐሳብ፣ ከድርጅቱን እየለቀቀች የምትገኘው ዩናይትድ ስቴትስ ከዚህኛው ምድብ ውስጥ መካተቷን የፍልስጤም ዜና አገልግሎት ዋፋ ዘግቧል፡፡

ከውሳኔ በኋላ የተናገሩት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፍልስጤም ቋሚ መልዕክተኛ ኢብራሂም ኽራይሺ፤ ውሳኔው “ተምሣሌታዊ ከመሆኑ በተጨማሪ ለጤና ጉዳዮች አስተዋጽኦ የምናበረክት የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አካል መሆናችንን የሚያረጋግጥ ነው” ብለውታል፡፡

ኽራይሺ አክለውም ፍልስጤም በቅርቡ በዓለም ጤና ድርጅት እና በሁሉም የተባበሩት መንግሥታት መድረኮች ውስጥ ሙሉ አባልነት ታገኛለች የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።

ውሳኔው የፍልስጤም ሕዝብ ዓለም አቀፍ የጤና ድጋፍ ተጠቃሚ እንዲሆን እንዲሁም ተገቢውን የጤና እንክብካቤ ለማቅረብ ዓለም አቀፍ የትብብር እና የቅንጅት አሠራሮችን እንዲያገኝ በማስቻል ወደፊት የሚያራምድ መሆኑ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ከዚህ በተጨማሪም ባለፈው ሣምንት በ78ኛ የዓለም ጤና ጉባኤ ወቅት የዓለም ጤና ድርጅት አባል አገራት ምሥራቅ ቁድስን ጨምሮ በወረራ በተያዘው የፍልስጤም ግዛት እንዲሁም የሶሪያ ጎላን ኮረብታ አካባቢ የሚስተዋለው አስከፊ የጤና ሁኔታ ላይ ሪፖርት ማድረጉን እንዲቀጥል በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ አባል ከሆኑት 193 አገራት መካከል 150 ገደማ ሀገሮች የፍልስጤምን ሀገርነት በይፋ ዕውቅና ሰጥተዋል። ሆኖም በምክር ቤቱ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ካላቸው መካከል ዩናይትድ ስቴትስ እና ብሪታንያ እስካሁን ድረስ ዕውቅና አልሰጡም፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular