በደቡብ ምሥራቅ እስያ ውስጥ የምትገኘው ማሌዥያ፤ የሐላል ኢንዱስትሪን ለማሳደግ ራሱን የቻለ ኮሚሽን ልታቋቁም መሆኑን የተናገሩት የሀገሪቱ ኢንቨስትመንት፣ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ናቸው፡፡ ሚኒስትሩ ቲንጉ ሴሪ ዛፍሩል ይህን የተናገሩት የደቡብ እስያ ሀገሮችን ባሳተፈው የአስያን (Association of Southeast Asian Nations) ፎረም ላይ ነው፡፡
በማሌዥያ መዲና ኳላላምፑር የተካሔደው ፎረም፤ ከዐሥሩ አባል ሀገሮች በተጨማሪ ቻይናን እንዲሁም ስድስት የገልፍ ትብብር ምክር ቤት ተወካዮችን ያሳተፈ ነው፡፡ ሐላል ኢንዱስትሪን በተመለከተ የተናገሩት ሚኒስትሩ፤ ከሀገሪቱ የሐላል ምክር ቤት የኮሚሽን ማቋቋሚያ ምክረ ሐሳብ መቅረቡን በመጠቆም በቀጣይ ጉዳዩ ወደ ካቢኔ እንዲመራ ከተደረገ በኋላ ውሳኔ እንደሚሰጥበት ገልጸዋል፡፡ ምክረ ሐሳቡ የሚቀርበው በሀገሪቱ የሐላል ምክር ቤት ሰብሳቢ ዳቱክ ሴሪ አሕመድ አማካኝነት እንደሚሆንም አስረድተዋል፡፡
የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት፤ የሐላል ኮሚሽን አቋቁማለሁ ባለችው ማሌዥያ እ.አ.አ በ2023 በሐላል ኢንዱስትሪ በድምሩ 54 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የወጪ ንግድ ግብይት ተካሄዷል፡፡ ይህ መጠን የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በማፋጠን ረገድ ወሳኝ ሚና መጫወቱን ባለሥልጣናት ይናገራሉ፡፡ ዘርፉ ለጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ወይም ጂዲፒ 10 በመቶ የሚገመት ድርሻ ማበረከቱም ተገልጿል፡፡
ባለሥልጣናት ማሌዥያ በአሁኑ ሰዓት በቀጣናው በሐላል ኢንዱስትሪ ፊት አውራሪ ሀገር መሆኗንም ይገልጻሉ፡፡ ለዚህ አስረጂ አድርገው የሚያቀርቡት በርካታ ሀገሮች ልምዶችን ለመቅሰምና ከዘርፉ ጋር ተያያዥ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ ለመተባበር ጥያቄ ማቅረባቸውን ነው።
እንደ ማሌዥያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ከሆነ፤ በአሁኑ ሰዓት በማሌዥያ ከሐላል ምግብ እና መጠጥ ባሻገር በመድኃኒት እና ሌሎች ዘርፎች ላይ ከፍተኛ ዕድገት እየተመዘገበ ነው፡፡ የኢንዱስትሪው አቅርቦት ከሙስሊም ሀገራት ባሻገር ሙስሊም ባልሆኑትም ጭምር ተመራጭ እየሆነ መጥቷል።
ከማሌዥያ በተጨማሪ በደቡብ ምሥራቅ እስያ ውስጥ የምትገኘው ኢንዶኔዥያ፤ የሐላል ኢንዱስትሪን ለማሳደግ ብሔራዊ እስላማዊ የፋይናንስ ማዕከል ማቋቋሟን ያስታወቀችው በተያዘው ዓመት መጀመሪያ ላይ ነበር፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ዕድገት እያስመዘገበ መሆኑ የሚነገርለት የሐላል ኢንዱስትሪ፤ በስሩ ሰባት ዘርፎችን የሚያቅፍ መሆኑ ይታወቃል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












