Homeዜናና ወቅታዊዜናየሃይማኖት ተቋማትን የሚያሳትፈው ሀገራዊ የምክክር አጀንዳዎችን የማሰባሰቢያ መድረክ በነገው እለት ሊጀመር ነው

የሃይማኖት ተቋማትን የሚያሳትፈው ሀገራዊ የምክክር አጀንዳዎችን የማሰባሰቢያ መድረክ በነገው እለት ሊጀመር ነው

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሃይማኖት ተቋማትን የሚያሳትፈው በፌደራል ደረጃ ካሉ የባለድርሻ አካላት ጋር የሚደረገው ሀገራዊ የምክክር አጀንዳዎችን የማሰባሰቢያ መድረክ፤ ነገ ጁመዓ ግንቦት 22/2017 እንደሚጀመር አስታወቀ፡፡

በአዲስ አበባ ሚሊንየም አደራሽ የሚከናወነው መድረክ ላይ፤ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን ተቋም የሚወክሉ ከወጣቶች፣ ከሴቶች፣ ከዑለማ እና ምሑራን የተመረጡ ግለሰቦች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ኮሚሽኑ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት የአጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረኩ ለሦስት ቀናት ማለትም ከግንቦት 22 እስከ 24/2017 የሚቆይ ነው፡፡

በመድረኩ ላይ 38 ገደማ ተቋማት እና ማኅበራትን የሚወከሉ ከ800 በላይ ወኪሎች የሚሳተፉ ይሆናል፡፡ ከሃይማኖት ተቋማት በተጨማሪ የሲቪል ማኅበራት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እና ሌሎች የባለድርሻ አካላት እንዲሳተፉ ጥሪ እንደተደረገላቸውም ተነግሯል፡፡

በዚህ መድረክ ላይ ተሳታፊ ከሚሆኑት መካከከል የኢትየጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አንደኛው ነው፡፡ የጠቅላይ ምክር ቤቱ የምክክር መድረክ አንደኛው አስተባባሪ ሐጂ ኑረዲን ጀማል በመድረኩ ላይ የሚሳተፉ ተወካዮችን እንዲልኩ ከኮሚሽኑ በቀረበው ጥያቄ መነሻ የተሳታፊዎችን መረጣ በማካሄድ ሥልጠና እንደሚሰጥ ለ“ሚንበር ቲቪ” ተናግረው ነበር፡፡

ግንቦት 16/2017 የተካሄደው የሥልጠና መድረክ/EIASC

በዚህም መሠረት ለተመረጡት ተሳታፊዎች ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ግንቦት 16/2017 ሥልጠና እንደተሰጠ ጠቅላይ ምክር ቤቱ ያወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡ በዚህ መድረክ ላይ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች አጀንዳዎች ለተሳታፊዎች ቀርበው ማብራሪያ እንደተሰጠም ተገልጿል፡፡ ማብራሪያ የተሰጠበት ከአንድ ዓመት በፊት ለምክክር ኮሚሽን የቀረበው የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን ጥያቄዎችን በያዘው ሰነድ፤ በአጀንዳነት የቀረቡት ጉዳዮች ዘጠኝ ናቸው፡፡

ግንቦት 16/2017 የተካሄደው የሥልጠና መድረክ/EIASC

እነዚህ አጀንዳዎች ታሪክና ትርክት፣ ሀገራዊና ሕዝባዊ ምልክቶች፣ የሲቪል መብቶችና ፍትሐዊ የሐብት ክፍፍል፣ የሕዳጣን (Minority) መብት፣ የኢትዮጵያ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አባል መሆን፣ የመንግሥትና ሃይማኖት ግንኙነት፣ ለሙስሊም ጠልነት ዕውቅና መስጠት እና ማስተካከል፣ የሕዝብና ቤት ቆጠራ እንዲሁም አካታች ኢኮኖሚና ፋይናንስ ማስፈን የሚሉት ናቸው።

በኢትዮጵያ በሚስተዋሉ ችግሮች ላይ ውይይት እያካሄደ የሚገኘው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ በታኅሣሥ 2014 በፀደቀ የማቋቋሚያ አዋጁ ላይ በተለያዩ የፖለቲካ እና የሐሳብ መሪዎች፣ በመንግሥት እንዲሁም በኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል፣ ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያሉ ልዩነቶችን ወይም የአለመግባባት መንስኤዎችን በትክክል የሚዳስሱ ጉዳዮችን እንደሚለይ አስፍሯል።

በታኅሣሥ ወር የተቀመጠለት የሥራ ዘመን በመጠናቀቁ ተጨማሪ አንድ ዓመት የተራዘመለት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው ምክክር የሚቀርቡ አጀንዳዎችን ከክልሎች እና ከከተማ አስተዳደሮች ሲያሰባስብ ቆይቷል። ከዐሥር ክልሎች፣ ከአዲስ አበባ እና ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የተሰበሰቡ የምክክር አጀንዳዎችን ከወራት በፊት የተረከበው ኮሚሽኑ፤ በፀጥታ ችግር ምክንያት የዘገየውን የአማራ ክልል ተመሳሳይ ክንውን ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡ የሀገራዊ ምክክር አጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረክ እስካሁን ድረስ በብቸኝነት ያልተካሄደው በትግራይ ክልል ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular