Homeዜናና ወቅታዊዜናበአሜሪካ በቀረበው የጋዛ ተኩስ አቁም የድርድር ሐሳብ መስማማቱን ሐማስ ገለጸ

በአሜሪካ በቀረበው የጋዛ ተኩስ አቁም የድርድር ሐሳብ መስማማቱን ሐማስ ገለጸ

የፍልስጤሙ ሐማስ በአሜሪካ በቀረበው የጋዛ ተኩስ አቁም ድርድር ሐሳብ መስማማቱን ያስታወቀው አዲስ ባወጣው መግለጫ ነው፡፡ ቡድኑ መስማማቱን የገለጸበት የድርድር ሐሳብ የቀረበው፤ በአሜሪካ የመካከለኛው ምሥራቅ ልዩ ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ አማካኝነት ነው፡፡

ሐማስ ከእስራኤል ጋር የሚደረገውን ድርድር በተመለከተ ባወጣው መግለጫ፤ ከስቲቭ ዊትኮፍ ጋር በስምምነት ውሉ “አጠቃላይ ማዕቀፍ” መስማማቱን በመግለጽ፤ በሠነዱ የተካተቱ ጉዳዮችን ዘርዝሯል፡፡

በሐማስ መግለጫ መሠረት በጋዛ ለስልሣ ቀን የሚዘልቅ ጊዜያዊ ተኩስ አቁም ሲደረግ፣ የእስራኤል ወታደሮች በወረራ ከያዙት የጋዛ መሬት እንዲያፈገፍጉ ተደርጎ ያልተቋረጠ ሰብዓዊ ድጋፍ ይቀርባል፡፡ በዚህ ስምምነት በሐማስ ስር የሚገኙ 10 ምርኮኞችም ይለቀቃሉ፡፡ የሚለቀቁት ምርኮኞች በሕይወት ያሉ ሲሆኑ፤ በምትኩ ቁጥራቸው በአደራዳሪዎች የሚወሰን ፍልስጤማውያን ከእስራኤል ማጎሪያዎች ነጻ ይወጣሉ፡፡

የተኩስ አቁም ከታወጀ በኋላ የጋዛን ጉዳዮች የሚያስተዳድር የባለሞያዎች ኮሚቴ ማዋቀርም የስምምነቱ አካል መሆኑን አናዶሉ ኤጀንሲ ዘግቧል፡፡

ከሐማስ መግለጫ ጎን ስለ ድርድሩ የተናገሩት የአሜሪካ የመካከለኛው ምሥራቅ ልዩ ልዑክ፤ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ከተደረገ ተደርጎ ግጭቱም በዘላቂነት መፍትሔ ያገኛል የሚል ከፍተኛ ተስፋ መሰነቃቸውን ተናግረዋል ሲል አልጀዚራ ዘግቧል፡፡ አክሲዮስ የተሰኘው የአሜሪካ የዜና ድረ ገጽ፤ ድርድሩ ከጫፍ ሊደርስ የቀረው የሁለቱ አካላት “ጥቂት መቀራረብ ብቻ” መሆኑን አንድ የዋይት ሐውስ ምንጭ መናገራቸውን አስነብቧል፡፡

ሐማስ በአሜሪካ በቀረበው የተኩስ አቁም የድርድር ሐሳብ መስማማቱን ከመግለጹ አስቀድሞ በዚህ ሣምንት መጀመርያ የድርድሩን ሒደት በተመለከተ የተጣረሱ መረጃዎች ወጥተው ነበር፡፡ በወቅቱ በወጡ ዘገባዎች ሐማስ ስምምነቱን ቢገልጽም፤ እስራኤል እና አሜሪካ ሐማስ ላይ ወቀሳ በመሰንዘር ውድቅ ማድረጋቸው ተዘግቦ ነበር፡፡

ድረ ገጹ ለድርድሩ ቅርበት አላቸው ያላቸውን አንድ ምንጭ ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ሰኞ እለት የተፈጠረው የመረጃ መጣረስ መነሻ በአሜሪካ የቀረበውን የድርድር ሐሳብ ተደራዳሪዎቹ ሐማስ፣ እስራኤል እና ራሷ አሜሪካ ትርጓሜ የሰጡበት መንገድ ነው፡፡

ከዚህ መረጃ መውጣት በኋላ በማግሥቱ ማክሰኞ የተፈጠረውን ብዥታ ለማጥራት በሚል የትራምፕ አስተዳደር አደራዳሪው የፍልስጤም የዘር ግንድ ያላቸው ባለሐብቱ ቢሻራ ባህባህ በዶሐ ከሐማስ ከፍተኛ መሪዎች ጋር ንግግር ሲያደርጉ፤ በአንጻሩ ስቲቭ ዊትኮፍ ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አማካሪ ሮን ደርመር ጋር በዋሺንግተን ተገናኝተው መክረዋል፡፡ የሐማስ መግለጫ የመጣው ከዚህ በኋላ መሆኑም በዘገባው ተጠቅሷል፡፡ ዊትኮፍ ጥቀት ቆይተው ወደ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ጽሕፈት ቤት በማምራት የስምምነቱ ሒደት የመጨረሻ ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቋሚ ንግግር አድርገዋል፡፡

በዚህ ዙር ድርድር ሐማስ በ60 ቀናት ጊዜያዊ የተኩስ አቁም በሚደረግበት ወቅት፤ በዘላቂነት ለማቆም ድርድር እንዲካሄድ መጠየቁ ተገልጿል፡፡ ቡድኑ ለዚህ መነሻ ያደረገው ከወራት በፊት ተግባራዊ የተደረገውን የተኩስ አቁም ስምምነት የእስራኤል ባለሥልጣናት በመጣስ ጥቃት መቀጠላቸው መሆኑንም ዘገባው አመልክቷል፡፡ በአሁኑ ድርድር ሐማስ ዋስትና እንዲሰጠው ጠይቋል ተብሏል፡፡

የእስራኤል ወታደሮች ባለፈው አንድ ዓመት ከመንፈቅ በጋዛ በሰነዘሩት መጠነ ሰፊት ጥቃት ቢያንስ 53 ሺሕ ፍልስጤማውያን መደገላቸውን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular