የሳዑዲ ዐረቢያ እና ግብጽን ጨምሮ የአራት ሙስሊም እና ዐረብ ሀገሮች ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፤ የፍልስጤም ግዛት ወደሆነው ዌስት ባንክ ሊያደርጉት የነበረው ጉዞ ግዛቱን በወረራ በያዙት የእስራኤል ባለሥልጣናት መደናቀፉ በሀገሮቹ ተቃውሞ ቀርቦበታል፡፡
የሳዑዲ ዐረቢያ፣ ግብጽ፣ ዮርዳኖስ እና ባሕሬን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፤ ወደ ዌስት ባንክ ተጉዘው ትናንት እሑድ በራማላህ ከፍልስጤም አስተዳደር ፕሬዝዳንት ማሕሙድ አባስ ጋር ለመወያየት ቀጠሮ ይዘው እንደነበር ሚድል ኢስት ዐይ ዘግቧል፡፡ ይሁን እንጂ የእስራኤል ባለሥልጣናት ከጉዞው አስቀድመው ሚኒስትሮቹ ወደ ከተማዋ እንደማይገቡ ክልከላ እንደሚጥሉ ዛቻ በመሰንዘራቸው ለማራዘም መገደዳቸውን የዮርዳኖስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ አመልክቷል፡፡
የሐገሮቹ ሚኒስትሮቹ በጋራ ባወጡት መግለጫ፤ ርምጃው የእስራኤል ባለሥልጣናት “እንደ ወራሪ ኃይል የተጣለባቸውን ግዴታ የጣሰ” መሆኑን በመጥቀስ ድርጊቱን አውግዘውታል፡፡ አክለውም ድርጊቱ “የእስራኤልን እብሪት፣ ለዓለም አቀፍ ሕግ ተገዢ አለመሆን እንዲሁም ቀጣይነት ያለው የሕገ ወጥ ፖሊሲ” ትግበራ ነጸብራቅ ነው ብለውታል፡፡
በሳዑዲ ዐረቢያ የፍልስጤም አምባሳደር በበኩላቸው፤ ጉብኝቱ የፍልስጤም ጉዳይ ለዐረቦችና ለሙስሊሞች ያለውን ጠቀሜታ ለማጉላት የታሰበ እንደነበር ለሀገራቸው መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል፡፡ በአንጻሩ እስራኤል ባለሥልጣናት ጉዞውን ለፍልስጤም ሀገረ መንግሥት ዕውቅና ለመስጠት የሚደረገው ሙከራ አካል ነው በሚል መቃወማቸው በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
ልዑካን ቡድኑን ይመሩታል ተብሎ የተጠበቀው የሳዑዲ ዐረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፈይሰል ቢን ፈርሐን፤ ወደ ዌስት ለመጓዝ የያዙት ዕቅድ የሚሳካ ከሆነ ከ60 ዓመታት በኋላ በወረራ የተያዘውን ፍልስጤምን የጎበኘ የመጀመሪያው የሀገራቸው ከፍተኛ ባለሥልጣን ያደርጋቸዋል፡፡ ወደ ዌስት ባንክ የሚደረገው ጉዞ መራዘሙ ቢገለጽም ቀጣይ ስለ ቀጣይ የጊዜ ሰሌዳው የተባለ ነገር የለም፡፡
የእስራኤል ባለሥልጣናት የዐረብ እና ሙስሊም ሀገሮችን ሚኒስትሮች ወደ ዌስት ባንክ እንዳይገቡ ክልከላ የጣሉት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በርካታ የአውሮፓ መንግስታት የሚደግፉትን ሁለት ሀገር የመመሥረት የመፍትሔ ሐሳብ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተስተጋባ ባለበት ሰሞን ነው፡፡ በሚቀጥለው ሰኔ ወር ሳዑዲ ዐረቢያ እና ፈረንሳይ በአሜሪካ ኒውዮርክ የወደፊት የፍልስጤም መንግሥትነት ዕቅድ ላይ ለመወያየት ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ በዚህ ኮንፍረንስ ላይ ፈረንሳይ ለፍልስጤም ሀገረ መንግሥት ዕውቅና የመስጠት ዕቅድ እንዳላት ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን መናገራቸው ይታወሳል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












