አያቴ ኸዲጃ አማር እ.አ.አ በግንቦት 1948 በይት ደራስ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቷ ለመጨረሻ ጊዜ ስትወጣ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን አብረዋት የነበሩ ቢሆንም ብቻዋን ነበረች። እነዚህ ሰዎች በጽዮናዊ ሚሊሻዎች ከተቃጣው አሰቃቂ ጥቃት ለማምለጥ የተምነሸነሸ ቤታቸውንና ቀዬ ጥለው የወጡ ናቸው። እነሱም ብቻቸውን ነበሩ። ይህ ሁሉ ሲፈፀም በዓለም ዙርያ የሚመለከታቸው አንድም ሰው አልነበረም። ኑሯቸው ከዓለም ጋር ባንድ ጥላ ስር ቢሆንም ለብቻቸው የቆሙ ነበሩ። በወቅቱ የደረሰባቸውን አሳዛኝ ሁኔታ ለመግለጽ የሚያስችል ቃል የለም።
ይህ ከተፈፀመ 77 ዓመት ደፍኗል። አስከፊው ነገር በአያቴ ላይ የተፈፀመው ነገር ዛሬም አለመቆሙ ነው። ከነዚህ ሁሉ ዓመታት በኋላ [ፍልስጤማውያን] በመሬታችን በክብር ለመኖር መሞከራችን ለስደት፣ ሞት እና ቅጣት ዳርጎናል።
ይህን ከሁለት ቀናት በፊት በአልጀዚራ የጻፉት በአልበርታ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሣይንስ ፕሮፌሰሯ ገዳ አጂል ናቸው። ፕሮፌሰሯ ፍልስጤማዊት ናቸው፤ የሦስተኛው ትውልድ ፍልሠተኛ ፍልስጤማዊት።
የገዳ አጂል አያት ኸዲጃ አማር ሰቆቃ የጀመረው ሜይ 15/1948 ነበር፡፡ በእስራኤል መሬታቸው በወረራ ተይዞ ጥቃት የሚፈራረቅባቸው ፍልስጤማውያን፣ ይህን ቀን መቅሰፍት (“ነክበህ”) ብለው ይጠሩታል፡፡ በየዓመቱ እየታሰበ ከሁለት ቀን በፊት 77 ዓመት ሞላው።
በወቅቱ አይሁዳዊያን በፍልስጤማዊያን ላይ ጦርነት ከፍተው በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ቀያቸውን ጥለው እንዲሸሹ አድርገዋል፡፡ የቀጠለው ጥቃት የፍልስጤማውያንን ስምንት ዐስርት ዓመታት የተጠጋ ኑሮ ተቆጣጥሮት ሕይወታቸውን በሰቆቃ እንደሞላው አለ።
በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ፍልስጤማውያን በመሬታቸው ላይ ለመንቀሳቀስ ጭምር ፍቃድ ሰጪው ሌላ ሆኗል፡፡ እስራኤል በተለይ ከ1995 ወዲህ በወረራ የያዘችውን ዌስት ባንክን በሦስት ክፍል በመሸንሸን በ700 ሺሕ ሠፋሪዎች ሞልታ ፍልስጤማውያን በአንድ አካባቢ እንዲወሰኑ አድርጋለች፡፡ በዌስት ባንክ እስራኤል የራሷን ሰዎች በሕገ ወጥ መንገድ ስታሠፍር ከዐስር ሺሕ በላይ የፍልስጤማውያን ግንባታዎችን አውድማ ነው፡፡
መሬታቸው ባዕድ የተወረረባቸው ፍልስጤማውያን፣ ወደ ሥራ ሊሄዱ ሲሉ የይለፍ ፍቃድ ለማግኘት በማለዳ መሰለፋቸውም የዕለት ውሏቸው አካል ሆኖ እነዚህ ሁሉ ዓመታት አለፉ፡፡ እስራኤል የፍልስጤማውያኑ እንቅስቃሴ ላይ ገደብ ጥላ ሥማቸው በሥራ ማጣት ከዓለም ሦስተኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ ሆኗል፡፡
እስራኤል የፍልስጤማዊያኑን ሰቆቃ የምታበረታው የንግድ እንቅስቃሴንም በማፈን ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ፍልስጤም ከአጎራባች ዐረብ ሀገራት ጋር የንግድ ግንኙነቷ ተቆርጧል፡፡ የወጪ እና ገቢ ንግዷም በእስራኤል በኩል እንዲያልፍ ጉልበተኛ ተሹሞበታል፡፡
እስራኤል በፍልስጤማዊያን ላይ የጣለችው ገደብ ወደ ቴክኖሎጂም የሚሻገር ነው፡፡ እስራኤል ለራሷ 5ጂ ኔትወርክ ስትጠቀም፣ ፍልስጤማውያኑ በ3ጂ ኔትወርክ እንዲወሰኑ ተደርገዋል፡፡ እስራኤል በገደብ የምትለቀውን ኔትወርክ ፍልስጤማውያኑን ለመሰለል ጥቅም ላይ የምታውለው ነው፡፡ ፍልስጤማውያን የኔትወርክ ብቻ ሳይሆን የንፁሕ መጠጥ ውሃ እና ሌሎች መሠረታዊ አቅርቦቶች ላይ ገደብ ተጥሎባቸዋል፡፡
ለ77 ዓመታት በወረራ በያዘችው መሬት ላይ የተሾመችው እስራኤል፣ ከባለፈው ዓመት ጥቅምት 2024 ወዲህ በንጹሐን ላይ የምትሰነዝረውን ሰብዓዊነት የጎደለው ጥቃት በመጠን አስፋፍታ እስከ ትናንት ጁመዓ ድረስ ቢያንስ 53 ሺሕ ሰዎችን መግደሏን የጋዜ ጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። ፍልስጤማዊያኑ መቅሰፍት ሲሉ የሚጠሩትን ቀን ሲያስቡ፣ በዓመታት ሰቆቃ ውስጥ ከአጠገባቸው የተለዩዋቸውን እያስታወሱ ነው። (ሚንበር ቲቪ)












