Homeዜናና ወቅታዊዜናበመጅሊስ ምርጫ ተመራጮች “የምረጡኝ ቅስቀሳ” ማድረግ እንደሌለባቸው የሚደነግግ ፈትዋ ተሰጠ

በመጅሊስ ምርጫ ተመራጮች “የምረጡኝ ቅስቀሳ” ማድረግ እንደሌለባቸው የሚደነግግ ፈትዋ ተሰጠ

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የዑለማ ጉባዔ፤ በቀጣይ በሚካሄደው የመጅሊስ ምርጫ ተመራጮች “የምረጡኝ ቅስቀሳ” ማድረግ እንደሌለባቸው በሰጠው ፈትዋ አስታውቋል፡፡ የዑለማ ምክር ቤቱ ፈትዋውን የሰጠው በጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት በቀረበለት ጥያቄ ላይ ተመርኩዞ መሆኑን ገልጿል፡፡

የዑለማ ምክር ቤቱ ይህን ያስታወቀው ዛሬ ሐሙስ ግንቦት 7/2017 በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላ ምክር ቤት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡ በመግለጫው ላይ ፈትዋ የሰጠው በቀጣይ ወራት ለሚካሄደው የመጅሊስ ምርጫ አፈጻጸም ዙሪያ “ሸሪዓዊ ዕይታ የሚገልጽ ማብራሪያ” እንዲሰጥ በደብዳቤ መቅረቡን የዑለማ ምክር ቤት አባላት ተናግረዋል፡፡

ስምንት አባላት ያሉት ኮሚቴ፤ “የምርጫን ሸሪዓዊ ድንጋጌውን (ሑክም) እና አፈጻጸሙን በመመርመር” በሰጠው ፈትዋ፤ ተመራጮች “የምረጡኝ ቅስቀሳ” ማድረግ እንደሌለባቸው በመግለጽ፤ “እንዲያውም ለሥልጣን መጓጓት አደገኛ መሆኑን በሰፊው ማስገንዘብ ይገባል” ብሏል፡፡ በፈትዋው ላይ በሸሪዓዊ ብይኑ መነሻ የምርጫውን መስፈርት እና ሥነ ሥርዐቱን የተመለከቱ ሌሎች ጉዳዮች ተዘርዝረዋል፡፡  

በዚህም ሸሪዓዊ ብይኑን በተመለከተ “በኢስላም መሪን መምረጥ” ተቀባይነት ያለው መሆኑ በተለያዩ የሸሪዓ ማስረጃዎች ተረጋግጧል ያለው የዑለማ ኮሚቴው፤ ምርጫ “ከተፈቀዱ ማኅበራዊ ጉዳዮችና ውሎች ውስጥ የሚመደብ” መሆኑንም ገልጿል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ምርጫ የሙስሊሙን ጥቅም ከማረጋገጥ አንጻር የሙስሊሞችን አንድነት በማስጠበቅ፣ የማበጣበጥ ፍላጎት ያላቸውን ወገኖች ሴራ በማስቆም፤ ይበልጥ ብቃት ያለውን መሪ በሕጋዊ መንገድ ለማምጣት እና የሥልጣን ሽኩቻና ፉክክር ለማስቆም ፍቱን ዘዴ እንደሆነም በተሠጠው ፈትዋ ላይ ሠፍሯል፡፡

የተመራጭ መስፈርትን በተመለከተም ተመራጭ ግለሰብ ታማኝ፤ ፍትሓዊ፣ ሃይማኖተኛ መሆን እንደሚኖርበት የሚገልጸው የዑለማ ኮሚቴ ፈትዋ፤ ሸሪዓውን በትክክል የሚያውቅ መሆን እንደሚኖርበት ከዘረዘራቸው መካከል አስቀምጧል፡፡ ምርጫው “በቡድን ወይም በመዘሀብ ወይም በስብስብ” መሆን እንደሌለበት ተገልጿል፡፡ ለዚህ በምክንያት ያስቀመጠው “በሙስሊሞች መካከል ክፍፍል፣ ግጭት እና ህብረተሰቡን ወደመፈረካከስ እንዳያመራ” ጥንቃቄ ለማድረግ መሆኑንም ይገልጻል፡፡ ከተመራጮች ባሻገር መራጮች “ኃላፊነት ሊሰማቸውና ለቦታው የሚመጥንን ሰው ለመምረጥ ለግለሰቦች ወይም ለቡድኖች ከመወገን ነጻ መሆን” እንደሚኖርባቸውም አስገንዝቧል፡፡

በዛሬው መግለጫ የተናገሩት የዑለማ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ እና የፈትዋ ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ ዶ/ር ጀይላን ኸድር፤‎ ‎በቀጣይ የሚደረገው የመጅሊስ ምርጫ፤ ለሙስሊሞች አንድነት ምክንያት የሚሆን እና ለችግሮች መፍትሄ የሚያመጣ እንዲሆን ዱዓችን ነው ብለዋል፡፡ ምርጫው ሁሉም የሚሳተፍበትና ያለምንም ልዩነት እና መገፋት ሁሉም ከመስጂዶቹ የሚመረጥበት እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡ በጠቅላይ ምክር ቤቱ የምርጫ መስፈርቶችን እና አፈጻጸሙ በተመለከተ ፈትዋ እንዲዘጋጅ ጥያቄ በመቅረቡ መዘጋጀቱንም አረጋግጠዋል፡፡

የምርጫ ፈትዋውን የሰጡት ዑለማዎች ዶ/ር ጄይላን ኸድር፣ ሸይኸ ዓብደላ ኢድሪስ፣ ዶ/ር ሙሐመድ ሐሚዲን፣ ዶ/ር ዓብደላ ኸድር፣ ዶ/ር ፈይሰል ሙሐመድ፣ ዶ/ር ከማል ገለቱ፣ ሸይኽ ዓብዱሰላም አንዋር እና ሸይኽ ሙሐመድዘይን ዘህረዲን መሆናቸው ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ለምርጫ ሸሪዓን መሠረት ያደረገ መመሪያ እንደሚያዘጋጅ ገልጾ ነበር፡፡ የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ ለዑለማ ምክር ቤት እና ለአማካሪዎች አጭር ጥናታዊ ጽሑፍ እንዲያቀርቡ የጠየቁት ነሐሴ 27/2016 ነበር፡፡

የጠቅላይ ምክር ቤቱ የወቅቱ ኃላፊዎች ወደ ሥልጣን የወጡት በሐምሌ 2014 እንደነበር ይታወቃል፡፡ የምክር ቤቱ የዑለማ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ ለአመራሮቹ የሰጠው የሥልጣን ጊዜ ሦስት ዓመት ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular