Homeዜናና ወቅታዊዜናአሕመድ አሸረዕ እና ትራምፕ በሪያድ

አሕመድ አሸረዕ እና ትራምፕ በሪያድ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሳዑዲ ዐረቢያ ይፋዊ ጉብኝት የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንን ትኩረት እንደሳበ ቀጥሏል፡፡ ፕሬዝዳንቱ በሀገሪቱ ቆይታቸው ከሳዑዲ ልዑል አልጋ ወራሽ ሙሐመድ ቢን ሰልማን ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ በውይይቱ ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል የሶሪያን ወቅታዊ ሁኔታ የሚመለከተው ይገኝበታል፡፡ በዚህም ሶሪያውያን በዚህ ውይይት ለመስማት የሚናፍቁት ዜና ደጃቸው ደርሷል፡፡ ይህን ዜና ትራምፕ የተናገሩት ለሙሐመድ ቢን ሰልማን ነው፡፡ ፕሬዝዳንቱ ሀገራቸው በሶሪያ ላይ የጣለችውን ማዕቀብ እንድታነሳ ትዕዛዝ እንደሚያስተላልፉ ይፋ አድርገዋል፡፡ ይህን የሚያደርጉት “ሶሪያ ዳግም ወደ ከፍታዋ እንድትመለስ ዕድል ለመስጠት” መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ትራምፕ የገቡትን ቃል የሚፈጽሙ ከሆነ ከቀድሞ ፕሬዝዳንት በሻር አል አሰድ አገዛዝ ማግሥት ላይ የምትገኘው ሶሪያ እ.አ.አ 1979 በኋላ ሙሉ ለሙሉ ከአሜሪካ ማዕቀብ ነጻ ትሆናለች፡፡ አሜሪካ በሀገሪቱ ላይ ማዕቀብ መጣል የጀመረችው የተሰናባቹ በሻር አል አሰድ አባት ሐፊዝ አል አሰድ የፕሬዝዳንት ሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ነው፡፡ ይህ ዜና ከተሰማ በኋላ ሶሪያውያን በደማስቆ ጎዳናዎች በመውጣት ደስታቸውን ሲገልጹ መታየታቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

ትራምፕ ማዕቀቡን እንደሚያነሱ ከተናገሩ በኋላ በዛሬው እለት ከሀገሪቱ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አሕመድ አሸረዕ ጋር በአካል ተገናኝተው ውይይት ማድረጋቸውን ፍራንስ 24 ዘግቧል፡፡ ትራምፕ ማዕቀቡን እንደሚያነሱ በተናገሩበት ወቅት አሕመድ አሸረዕ ከሚመሩት መንግሥት አዲስ ነገር እንደሚጠብቁ በመጠቆም መልካም እድል ተመኝተው ነበር፡፡

ፕሬዝዳንቱ በቆይታቸው በገልፍ ፎረም እና በሳዑዲ አሜሪካ ኢንቨስትመንት ፎረም ላይ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ በተለይ በሳዑዲ አሜሪካ ኢንቨስትመንት ፎረም ላይ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያስገኛሉ የተባሉ ሰምምነቶች መደረጋቸውን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡ በፎረሙ ላይ የፕሬዝዳንቱ የቅርብ ሰው የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪ አምራቹ ቴስላ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቱጃሩ ኤሎን መስክን ጨምሮ በርካታ የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች መሪዎች ተገኝተዋል፡፡ ኤሎን መስክ በዚህ ፎረም ላይ በሰው ቅርጽ የሚሠራውን ሂዩማኖይድ ሮቦትን የተመለከተ ንግግር አድርጓል፡፡ እነዚህን ሮቦቶች መጠቀም ከተቻለ ዓለም አሁን ካለው በ10 እጥፍ የሚበልጥ ኢኮኖሚያዊ እድገት ልታስመዘግብ ትችላለች የሚል ሐሳብ አንስቷል፡፡

መስክ ከዚህ በተጨማሪም በግሉ የሚተዳደረውን የሳተላይት ኢንተርኔት አገልግሎት ሰጪው ስታርሊንክ ኩባንያ በሪያድ ተቀባይነት ማግኘቱን በመናገር፤ በሮቦት የሚታዘዙ ታክሲዎች በሀገሪቱ ውስጥ በሥራ ላይ እንዲውሉ ምኞት እንዳለው ገልጿል፡፡

ትራምፕ የሳዑዲ ቆይታቸው ሲጠናቀቅ የሚበሩት ወደ ኳታር ዶሐ ነው፡፡ በመቀጠል ወደ ዱባይ ይጓዛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በዚህ መሃል የውጭ ጉዳይ ሚኒትራቸው ማርኮ ሩብዮ የባህረ ሰላጤ ሀገራት ጉብኝታቸው ከመጠናቀቁ አስቀድሞ ወደ ቱርክ እንደሚጓዙ ተናግረዋል፡፡ ትራምፕ ሚኒስትሩን ወደ ቱርክ የሚልኩት የሩስያ እና የዩክሬን መሪዎችን ለማወያየት መሆኑን የሚድል ኢስት አይ ዘገባ አመልክቷል፡፡ የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ከዚህ አስቀድሞ ነገ ሐሙስ የኔቶ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር እንደሚመክሩ አስታውቋል፡፡ ዋይት ሐውስ እንዳላው ከሆነ፤ ሩቢዮ ወደ ቱርክ የሚጓዙት የሀገሪቱን የመካከለኛው ምሥራቅ ልዩ ልዑክ ስቲቭ ዊኮፍ እና ኪት ኬሎግን አስከትለው ነው፡፡

በአንካራ በሚደረገው ውይይት ላይ የሩስያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እንደሚሳተፉ ማረጋገጫ ባይሰጡም፤ ከሀገሪቱ ጋር ጦርነት ውስጥ የቆየችው የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ሐሙስ ወደ ከተማዋ ተጉዘው ከቱርክ ፕሬዝዳንት ረጀብ ጠይብ ኤርዶጋን ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ ለጋዜጠኞች መናገራቸው በዘገባው ተጠቅሷል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular