Homeዜናና ወቅታዊዜናቀዳሚዎቹ ኢትዮጵያውያን ሑጃጅ መዲና ገቡ

ቀዳሚዎቹ ኢትዮጵያውያን ሑጃጅ መዲና ገቡ

በዘንድሮ ዓመት በሐጅ ሥነ ሥርዐት ላይ የሚሳተፉ ኢትዮጵያውያን ሑጃጅ ዛሬ ረቡዕ ግንቦት 6/2017 ማለዳ ሳዑዲ ዐረቢያ መዲና ከተማ መድረሳቸውን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አስታውቋል፡፡ መዲና የደረሱት ምዕመናን ንጋት ላይ በሳዑዲ ዐረቢያ አየር መንገድ በረራ ያደረጉ መሆናቸው ታውቋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ሑጃጅ ከሳዑዲ አየር መንገድ በተጨማሪ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመብረር በዝግጅት ላይ እንደሚገኙም “ሚንበር ቲቪ” ተረድቷል፡፡ በዛሬው በረራ በአጠቃላይ 448 ሑጃጅ ሳዑዲ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በቀዳሚው የሳዑዲ አየር መንገድ 180 ምዕመናን የበረሩ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል 268 ሑጃጅ የሚሳፈሩ ይሆናል፡፡

ለአስር ቀናት በሚቆየው በረራ በአጠቃላይ ስድስት ሺሕ ሑጃጅ በሥነ ሥርዐቱ ላይ ለመሳተፍ ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ ይጓዛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከእነዚህ መካከል በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል የሚበሩ ሑጃጅ ቁጥር አራት ሺሕ፤ በሳዑዲ አየር መንገድ ደግሞ ሁለት ሺሕ እንደሚሆን የጠቅላይ ምክር ቤቱ የሐጅ እና ዑምራ ዘርፍ ኃላፊ ሐጂ ዐብዱልፈታህ ሙሐመድ ናስር ለ“ሚንበር ቲቪ” ቀደም ብለው ገልጸዋል፡፡

ማለዳ ላይ ከቦሌ አየር መንገድ በጠቅላይ ምክር ቤቱ ሽኝት የተደረገላቸው ሑጃጅ መዲና ከተማ በሚገኘው ልዑል ሙሑመድ ቢን አብዱልዐዚዝ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ አቀባበል እንደተደረገላቸው ጠቅላይ ምክር ቤቱ ዛሬ ረፋድ ያወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

የፎቶ ምንጭ፡ የኢ/እ/ጉ/ጠ/ም/ቤት

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular