‘ሙሐመድ ቢን ሰልማን ከችግር ፈጣሪነት ወጥተው የሰላም ዘብ እየሆኑ ነው’
ይህ የተነበበው ባለፈው ሣምንት ለንባብ በበቃው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ይንጸባረቅበታል በሚባለው ዘ ኢኮኖሚስት መጽሔት ነው፡፡ መጽሔቱ ሳዑዲ ዐረቢያን በተመለከተ ይዞ በወጣው ዘገባ፤ ስለ መሪዋ ልዑል አልጋ ወራሽ ሙሐመድ ቢን ሰልማን በጎ ነገሮችን አስፍሯል፡፡ በነዳጅ ምርት የምትታወቀው ሀገራቸው በቅርብ ጊዜያት በዩክሬን የተኩስ አቁም፣ በአሜሪካ እና ኢራን ድርድር፣ በጋዛ ተኩስ አቁም ላይ የወሰደችውን ሚና ዘርዝሯል፡፡ ሳዑዲ በየመን ከሑውሲ ጋር ሀገራትን ማደራደሯ እንዲሁም ለአዲሱ የሶሪያ አስተዳደር ሀገሪቱ የነበረባትን የዓለም ባንክ ዕዳ በመክፈል እፎይታ እንዲያገኝ ማድረጓም በውዳሴ ቀርቧል፡፡
ዘ ኢኮኖሚስት ይህን ውዳሴ ሲያስነብብ በቀጣይ ቢን ሰልማን ይጠበቅባቸዋል ያለውንም ጽፏል፡፡ ይህ የተነበበው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለጉብኝት ሳዑዲ ዐረቢያ እንደሚጓዙ በሚነገርበት ዋዜማ ነበር፡፡ ይህንኑ ተከትሎ ትራምፕ ዛሬ ሰኞ ረፋድ ላይ ሪያድ ከተማ ደርሰዋል፡፡ ይህ ጉዞ ለትራምፕ ወደ ሥልጣን ከተመለሱ ወዲህ የመጀመሪያ ተብሎ ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡
በርግጥ ትራምፕ ሳዑዲ ከመድረሳቸው አስቀድሞ ወደ ሮም ተጉዘው ነበር፡፡ ነገር ግን በዲፕሎማሲ ግዳጅ የተደረገ ስለነበረ የሳዑዲ በረራቸው እንደመጀመሪያ የሚወሰድ መሆኑን አልጀዚራን ጨምሮ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ ሪያድ የደረሱት የቀድሞ አሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ያስለመዱትን ልማድ በመጣስ ነው፡፡ የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች ከሥልጣን ማግሥት የሚያቀኑት ዩናይትድ ኪንግደም፣ ሜክሲኮ አልያም ካናዳ ነበር፡፡ ትራምፕ ከስምንት ዓመት በፊትም ይህንኑ ልማድ ጥሰዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ሪያድ ከተማ ሲደርሱ በ‘ዘ ኢኮኖሚስት’ ሰላም ዘብ ተብለው የተጠሩት ሙሐመድ ቢን ሰልማን የሞቀ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡ መሪዎቹ ተገናኝተው በሐምራዊ ስጋጃ ሲራመዱ የታዩትም በብዙ አጀብ ነው፡፡
የትራምፕ የሳዑዲ ጉብኝት ለሦስት ቀናት በባሕረ ሰላጤ ሀገራት የሚያደርጉት ጉዞ አካል ነው፡፡ ኳታር እና የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የፕሬዝዳንቱ ቀጣይ መዳረሻ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በዚሁ ጉዞ በገልፍ ጉባኤ ላይ ይሳተፋሉ ተብሎ ቀጠሮ ተይዞላቸዋል፡፡ ከሙሐመድ ቢን ሰላማን ጋር የሚኖራቸው ውይይት በሥፋት ያተኩራል ተብሎ የሚጠበቀው በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚሆን የሬውተርስ ዘገባ ያመለክታል፡፡ ሀገሪቱ ከእስራኤል ጋር ያላትን ግንኙነት የሚመለከተው ጉዳይ በዚህ ዙር እምብዛም ትኩረት እንደማይሰጠው ዘገባዎች ይጠቁማሉ፡፡ ትራምፕ በሪያድ ቆይታቸው በሳዑዲ አሜሪካ ቢዝነስ ፎረም ላይ ይሳተፋሉ፡፡ በዚህም ሳዑዲ ዐረቢያ በዩናይትድ ስቴትስ የአንድ ትሪሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ውል እንድትፈጽም የማድረግ እቅድ ማሳካት ይፈልጋሉ ተብሏል፡፡ የሳዑዲ የጦር መሣሪያ ግዢ በጎን መነሳቱ እንደማይቀር የአልጀዚራ ዘገባ ጠቁሟል፡፡
ትራምፕ በሳዑዲ ዐረቢያ የሚያደርጉትን ቆይታ ሲያጠናቅቁ ወደ ኳታር ተጉዘው በወታደራዊ፣ ቀጣናዊ እና ሶሪያን በተመለከተ ከሀገሪቱ አሚር ሸይኽ ተሚም ቢን ሐማድ አስሳኒ ጋር እንደሚመክሩ ይጠበቃል፡፡ ሐሙስ በመጨረሻ ጉዞ እግራቸው በሚረግጥባት የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ከፕሬዝዳንት ሙሐመድ ቢን ዛይድ አል ነህያን ጋር በቴክኖሎጂ ዙርያ ውይይት ያደርጋሉ ተብሏል፡፡ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በዚህ ዙር እስራኤልን የመጎብኘት ፍላጎት እንደሌላቸው ተገልጿል፡፡ አክሲዮስ የተሰኘው የአሜሪካ ድረ ገጽ አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን ትራምፕ በዚህ ሰዓት እስራኤልን መጎብኘት “ምንም የሚያስገኘው መልካም ነገር የለም” ማለታቸውን አስነብቧል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












