በዘንድሮ ዓመት በሐጅ ሥነ ሥርዐት ክንውን ላይ ለመሳተፍ ከተመዘገቡ መካከል 448 ምዕመናን በመጪው ረቡዕ ወደ መዲና እንደሚጓዙ፤ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሐጅ እና ዑምራ ዘርፍ ኃላፊ ለ“ሚንበር ቲቪ” ተናግረዋል። በመጀመሪያ ቀን በረራ ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ መዲና ከተማ የሚጓዙ ኢትዮጵያውያን ቁጥር 448 መሆኑ ተገልጿል።
የጠቅላይ ምክር ቤቱ የሐጅ እና ዑምራ ዘርፍ ኃላፊ ሐጂ ዐብዱልፈታህ ሙሐመድናስር እንደተናገሩት፣ ረቡዕ ግንቦት 6/2017 የሚደረገው የሑጃጅ በረራ በሁለት አየር መንገዶች የሚከናወን ነው። አየር መንገዶቹ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የሳዑዲ ዐረቢያ አየር መንገድ ይሆናሉ። በኢትዮጵያ አየር መንገድ በዕለቱ በረራ ያደርጋሉ ተብሎ የሚጠበቀው ሑጃጅ ቁጥር 268 ሲሆን፣ ቀሪዎቹ 180 ምዕመናን በሳዑዲ አየር መንገድ የሚጓዙ ይሆናል።
በዕለቱ ቀዳሚውን በረራ ንጋት ላይ የሚያደርጉት በሳዑዲ አየር መንገድ የሚሳፈሩ ይሆናሉ። ረፋድ ላይ በሚደረገው በኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚጓዙ ሑጃጅ ሽኝት መርሐ ግብር በጠቅላይ ምክር ቤት መዘጋጀቱ ታውቋል። መዳረሻውን ቅድስቲቱ መዲና ከተማ የሚያደርገው በረራ ለተከታታይ አስር ቀናት እንደሚቀጥል ሐጂ ዐብዱልፈታህ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በሐጅ ሥነ ሥርዐት ላይ እንዲሳተፉ ምዝገባ ያከናወነው ለስድስት ሺሕ ምዕመናን ነው።
ከመላው ዓለም በሐጅ ሥነ ሥርዐት ላይ የሚሳተፉ ምዕመናን ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ መግባት ከጀመሩ ሁለት ሣምንት ተቆጥሯል። በሥነ ሥርዐቱ ላይ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ምዕመናን ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ቀደም ብለው የወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ። (ሚንበር ቲቪ)












