“አንዲት ትንሽ ልዕልት ዓለማችንን አፈካችው። አላህ (ሱ.ወ) ልጅ ሰጥቶ ስላከበረን ምሥጋና ይግባው፡፡ በወጉ ያሳድጋትና የደስታችን ምንጭ ያድርጋት”
ይህ የተጻፈው በፍልስጤማዊው ጋዜጠኛ የሕያ ሰቢህ ነው፡፡ ጋዜጠኛው ይህን በማኅራዊ ሚዲያ ላይ ያሠፈረው የመጀመሪያ ልጁን መወለድ ለማብሰር ነው፡፡ በጋዛ የሚኖረው የሕያ የልጁን ወደ ምድር መምጣት ዜና ለዓለም ካደረሰ በኋላ በአቅራቢያው ወደሚገኘው አንድ ሆቴል አመራ፡፡ ያመራበት ሆቴል የሚገኝበት አካባቢ የገበያ ሥፍራ በመያዙ ሕዝብ የሚበዛበት ነው፡፡ የጋዛ አክቲቪስቶችና የሞያ ባልደረቦቹ ፈጣን ኢንተርኔት ስለሚያገኙ ይመርጡታል ይባላል፡፡

ጋዜጠኛው እዚያው ሆቴል በተቀመጠበት ያለፉትን ሣምንታት በጋዛ የሚፈጽመውን ጥቃት የቀጠለው የእስራኤል ጦር ትናንት ረቡዕ ኢላማ አደረገው፡፡ በዚህም በሥፍራው የነበሩ በርካታ ንጹሐን ገደሉ፡፡ ዋፋ እንደዘገበው ቢያንስ 32 ንጹሐን ሲገደሉ፤ 86 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል፡፡ ከሟቾቹ መካከል ከሰዓታት በፊት ለዓለም የልጁን መወለድ ያበሰረው ጋዜጠኛ የሕያ ሰቢህ ተገኘ፡፡ የሕያ ‘ልዕልቴ’ ያላት ልጁን ተክቶ እርሱ እንደ ሌሎች ፍልስጤማውያን ሰማዕት ሆነ፡፡
የእስራኤል ወታደሮች ትናንት ረቡዕ ብቻ በተለያዩ የጋዛ ሠፈሮች በሰነዘሩት የአየር ጥቃት ከ100 በላይ ሰዎችን መግደላቸውን ሚድል ኢስት ዐይ ዘግቧል፡፡ እንደ ዘገባዎች ከሆነ፤ በፍልስጤም መሬት ውስጥ ከባለፈው ዓመት መጀመሪያ አንስቶ የተገደሉ ጋዜጠኞች ቁጥር የሕያን ጨምሮ 214 ደርሷል፡፡

በጋዛ የሚገኘው የመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ቢሮ ለተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ ሲያቀርብ የቆየውን የጋዜጠኛ የሕያ ሰቢህን ግድያ በማውገዝ ባወጣው መግለጫ፤ የዓረብ ጋዜጠኛች ፌዴሬሽንን ጨምሮ በመላው ዓለም የሚገኙ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቾች በከተማዋ በጋዜጠኞች ላይ የሚፈጸመውን ወንጅል እንዲያወግዙ ጥሪ አቅርቧል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












