Homeዜናና ወቅታዊሰሞነኛ ጉዳዮችየኦቲዝም እክል ያለበት የዐስር ዓመት ታዳጊ የቁርኣን ሒፍዝ አጠናቀቀ

የኦቲዝም እክል ያለበት የዐስር ዓመት ታዳጊ የቁርኣን ሒፍዝ አጠናቀቀ

ማሌዥያዊው የአስር ዓመት ታዳጊ አሕመድ ዚያድ ሙሐመድ፣ የቁርኣን ሒፍዝ አጠናቋል። ይህ ታዳጊ በአንጎል ዕድገት ውስንነት የሚከሰተው የኦቲዝም እክል እንዳለበት የታወቀው በሰባት ዓመት ዕድሜው ነበር።

የታዳጊው እናት ኑረል ሸሒዳ ሉቅማን፣ ልጇ አሕመድ ሒፍዙን ያጠናቀቀው፣ በማራንግ በሚገኘው በአማሊላህ የቁርኣን አካዳሚ ውስጥ እንደሆነ ተናግራለች።

እናት እንደተናገረችው፣ አሕመድ የቁርኣን ጥናት ፍላጎት ያሳደረው ገና በሕፃንነቱ ነበር። በዚህም ገና የሁለት ዓመት ከስምንት ወር ሕፃን እያለ 42 የቁርኣን አንቀጽ በቃሉ መያዝ ችሏል። የስምንት ወር ጨቅላ እያለ ደግሞ እንቅልፍ እንዲተኛ ቁርኣን እንዲያደምጥ ታደርግ እንደነበርም ታስታውሳለች።

በዚህ ጊዜ አንዳንድ አንቀጾችን በተሳሳትኩ ጊዜ በድጋሚ እንድቀራው በመፈለግ በሚመስል ስሜት ያለቅስ ነበር ብላለች። ይህን ፍላጎቱን ከግብ ለማድረስ ከባለቤቷ ጋር ተነጋግረው ከሚኖሩበት ከተማ በመቀየር አሁን ጥናቱን ያጠናቀቀበት የቁርኣን አካዳሚ እንዲገባ ማድረጋቸውን ለመገናኛ ብዙኃን አስረድታለች።

በአካዳሚው ውስጥ የሚያስተምረት ኑርፋቲሐር ሪድዋን፣ አሕመድ በማዕከሉ ውስጥ ከፍተኛ ብቃት ካላቸው ተማሪዎች መካከል ከፊት ረድፍ የሚሰለፍ መሆኑን ተናግረዋል። ችሎታውን ሲያስረዱም አንድ ገጽ ቁርኣን በሠላሳ ደቂቃ ውስጥ በቃሉ የመያዝ ችሎታ ያለው ነው ብለዋል።

ማሌዥያዊው የቁርኣን ሐፊዝ የገጠመው ኦቲዝም፣ ዘላቂ የአዕምሮ እድገት ውስንነት እክል መሆኑን የሕክምና ባለሞያዎች ይናገራሉ፡፡ ኦቲዝም አንዳንድ ሕፃናትን ከማኅበራዊ ሕይወት በመነጠል ያልተለመደ ባሕርይ እንዲያሳዩ ያደርጋቸዋል ይባላል፡፡

የኦቲዝም እክል ያለባቸው አንዳንድ ሕፃናት ያልተለመደ ባሕርይ ቢያሳዩም፤ ለየት ያለ የመማር ችሎታ ያላቸውና የመረዳት ክሕሎታቸው የላቀ እንደሆነም ሐኪሞች ይናገራሉ፡፡ (ሚንበር ቲቪ)


RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular