Homeዜናና ወቅታዊዜናየአል ነጃሺ መስጂድ ዕድሳት በተያዘው ወር ይጠናቀቃል ተባለ

የአል ነጃሺ መስጂድ ዕድሳት በተያዘው ወር ይጠናቀቃል ተባለ

በትግራይ ክልል የሚገኘው የአል ነጃሺ መስጂድ ዕድሳት በተያዘው ወር እንደሚጠናቀቅ “ሚንበር ቲቪ” ሰምቷል፡፡ በመስከረም ወር አጋማሽ የተጀመረው የመስጂዱ ዕድሳት ቀድሞ በተቀመጠለት የጊዜ ሠሌዳ መሠረት ተጠናቆ ከአሠሪው አካል ጋር ርክክብ እንደሚደረግ የተናገሩት በሥራው የተሳተፉ ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ባለሞያ ናቸው። እንደ ባለሞያው ከሆነ፤ የመስጅዱ ዕድሳት ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረው በስምንት ወራት ውስጥ ነው።

የመስጂድ ዕድሳቱ በክልሉ በነበረው ጦርነት ጉዳት ያስተናገደውን የመስጂዱን ውስጠኛ ክፍል እንዲሁም በዝናብ እና በሌላ  ምክንያት የተጎዳውን ያካተተ መሆኑ ታውቋል፡፡

የዕድሳት ሥራው የተከናወነው በትግራይ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ እንዲሁም የገንዘብ ድጋፍ በሚያደርገው በቱርክ የልማት ትብብር ኤጀንሲ (ቲካ) አማካኝነት መሆኑ ቀድሞ መገለጹ ይታወሳል፡፡ ሥራው በዋነኝነት በሁለቱ አካላት ትብብር የተከናወነ ቢሆንም የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እና የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት እንዲሁም የኢፌዴሪ ቱሪዝም ሚኒስቴር ተሳታፊ ሆነዋል።

የግንባታውን ወጪ የሸፈነው የቱርክ የልማት ትብብር ኤጀንሲ፤ በሀገሪቱ የባሕል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር ውስጥ የሚገኝ የልማት መምሪያ ነው፡፡ ኤጀንሲው ከዚህ ቀደም በተመሣሣይ የመስጂዱን ዕድሳት ለማከናወን እየሠራ በነበረበት ወቅት፤ በክልሉ ጦርነት በመከሰቱ ምክንያት ሥራውን ማቆሙ የተነገረ ነው፡፡ በ2013 በክልሉ በነበረው ጦርነት ወቅት በመስጂዱ ላይ ጉዳት መድረሱን ተከትሎ ዕድሳቱን በድጋሚ ለማከናወን፤ ከአንድ ዓመት በፊት ከትግራይ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን ስምምነት በማድረግ ሥራው ተጀምሯል።

መስጅዱ በጦርነቱ ወቅት ጉዳት ያስተናገደው በውስጠኛው ክፍል፣ በነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ባልደረቦች መቃብር እና በእልፍኙ ነበር፡፡ በተከናወነው የዕድሳት ሥራ እነዚህን ጨምሮ በዝናብ እና ሌሎች ሁኔታዎች የደረሰው ጉዳት ተጠግኗል።

ዕድሳት የተከናወነለት አል ነጃሺ መስጅድ፤ ከትግራይ ክልል ዋና መቀመጫ መቐለ ከተማ በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ነው፡፡ በአራት ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈው አል ነጃሺ መስጅድ፤ ዋናውን መስጂድ እንዲሁም ሁለት የቀብር ሥፍራዎችን በውስጡ ይዟል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular