Homeዜናና ወቅታዊዜናየፓኪስታን የሐጅ ወኪሎች የሑጃጅ ክፍያ ገንዘብ ወደተሳሳተ አካውንት መተላለፉ በሀገሪቱ ፓርላማ ጥያቄ...

የፓኪስታን የሐጅ ወኪሎች የሑጃጅ ክፍያ ገንዘብ ወደተሳሳተ አካውንት መተላለፉ በሀገሪቱ ፓርላማ ጥያቄ አስነሳ

የፓኪስታን ፓርላማ የሐጅ ወኪሎች በዘንድሮ የሐጅ ሥነ ሥርዐት ላይ ለመሳተፍ የተዘመገቡ የ67 ሺሕ ሑጃጅ ክፍያ ገንዘብ ወደተሳሳተ አካውንት እንዲተላለፍ ማድረጋቸው ላይ ጥያቄ አንስቷል፡፡

ወኪሎቹ ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ ይፋዊ የሐጅ ክፍያ መግባት የነበረበትን 60 ሚሊዮን የሳዑዲ ዐረቢያ ሪያል ያስገቡት፤ በዓለም የነዳጅ ላኪዎች ማኅበር (ኦፔክ) አካውንት መሆኑ በፓርላማ ተገልጿል፡፡

በወኪሎቹ የተፈጸመው ስሕተት በፓርላማ ይፋ በተደረገበት ወቅት የተናገሩት የፓኪስታን ብሔራዊ ጉባኤ የሃይማኖት ጉዳዮች ሰብሳቢ ማሊክ አሚር፤ የተፈጸመውን ስሕተት በፓኪስታን የሐጅ ታሪክ ውስጥ “እጅግ አስከፊው ቅሌት ነው” ብለውታል፡፡ ሰብሳቢው ለተፈጠረው ስሕተት ተጠያቂነት እንዲሰፍን ጠይቀዋል፡፡ አክለውም በተፈጠረው ስሕተት ምክንያት ሀገራቸው በዘንድሮ ዓመት የተመደበላትን ኮታ ሙሉ ለሙሉ ላትጠቀም እንደምትችል ጥቆማ ሰጥተዋል፡፡

በአንጻሩ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ሸሕባዝ ሸሪፍን ያካተተ ኮሚቴ ተዋቅሮ ጉዳዩ እንዲጣራ ምክረ ሐሳብ አቅርቧል፡፡ የግል ወኪሎች ማኅበር ተወካይ ጉዳዩ በፓርላማ ላይ በተሰማበት ወቅት የፓኪስታን የሃይማኖት ጉዳዮች ሚኒስቴር ለመንግሥት ወኪሎች ያደላ አሠራር ዘርግተው የግል ወኪሎችን በድለዋል የሚል ክስ አቅርበዋል፡፡

በዘንድሮ ዓመት በሐጅ ለሚሳተፉ የፓኪስታን ዜጎች የተሰጠው ኮታ 179 ሺሕ 210 ነው፡፡ ሀገሪቱ በጥር ወር ከሳዑዲ ዐረቢያ የሐጅ እና ዑምራ ሚኒስቴር ጋር ስምምነት ከተፈራረመች በኋላ 90 ሺሕ ምዕመናን በመንግሥት አማካኝነት ለመጓዝ ሲደለደሉ፤ ቀሪው ለግል ወኪሎች የተሰጠ እንደነበር የዐረብ ኒውስ ዘገባ ያመለክታል፡፡ ይሁን እንጂ በተፈጠረው የአሠራር ክፍተት በግል ወኪሎች ሊጓዙ የሚችሉት 23 ሺሕ ምዕመናን ብቻ እንደሚሆኑ ተገልጿል፡፡

በፓኪስታን ለዘንድሮ ዓመት ሐጅ ሥነ ሥርዐት የተመዘገቡ ምዕመናን የመጀመሪያ ጉዞ የሚያደርጉት በቀጣይ ሣምንት ማክሰኞ ነው፡፡

ለ1446 ዓ.ሂ የሐጅ ሥነ ሥርዐት ክንውን ከመላው ዓለም ባለፉት ዓመታት ከተመዘገበው በላይ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ምዕመናን ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የሳዑዲ ዐረቢያ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡(ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular