በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ስር የተመሠረተው የኢትዮጵያ ሙስሊም ወጣቶች ካውንስል፤ ይፋዊ የምሥረታ መርሐ ግብሩን በአዲስ አበባ ከተማ ለማከናወን ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡ በሚሊኒየም አዳራሽ የሚካሄደው መርሐ ግብር ሚያዝያ 26/2017 የሚደረግ መሆኑን የካውንስሉ አመራሮች በዛሬው እለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል፡፡
በጠቅላይ ምክር ቤቱ አዳራሽ በተሰጠው መግለጫ ላይ የካውንስሉ ፕሬዝዳንት ኡስታዝ ሐይደር ኸድር፣ የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ኃላፊ ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ እንዲሁም ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
የወጣት ካውንስሉ ፕሬዝዳንት ኡስታዝ ሐይደር፤ በእለቱ ከጧት አንስቶ በሚኖረው መርሐ ግብር ላይ ከተለያየ የሀገሪቱ ከፍል ዑለማዎች፣ የማኅበረሰብ መሪዎች፣ ምሑራን፣ የሲቪክ ተቋማት መሪዎች፣ የመንግሥት ተወካዮች፣ ዱዐቶች እና መሻኢኾች፣ ወጣቶችና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ በዕለቱ ካውንስሉ እስካሁን ድረስ ያከናወናቸውን ሥራዎች ጨምሮ የወደፊቅ እቅዱ ይፋ እንደሚደረግም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል፡፡
በመግለጫ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤቱ የፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ፤ የኢትዮጵያ ሙስሊም ወጣቶች ለዲኑና ለዑማው ትልቅ ሥራ እንዲሠሩ ለማስቻል መቀናጀትና በአንድነት መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል። በወጣቶቸ ካውንስል ምስረታ መርሐ ግብር ላይ ወጣቶች በጋራ ለመሥራት አብሮ ቃል ኪዳን የሚፈጽሙበት እንደሚሆንም በመግለጽ እገዛ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፤ የኢትዮጵያ ሙስሊም ወጣቶች ካውንስል ምሥረታን ይፋ ያደረገው ኅዳር 5/2017 ነበር። (ሚንበር ቲቪ)












