Homeዜናና ወቅታዊዜና“በእስያ በተፈጸመ የሣይበር ውንብድና የ37 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ ደርሷል” - የተመድ ሪፖርት

“በእስያ በተፈጸመ የሣይበር ውንብድና የ37 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ ደርሷል” – የተመድ ሪፖርት

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፤ መሠረታቸውን ከእስያ አሕጉር ያደረጉ የሣይበር ወንጀሎችን መጠንቀቅ እንደሚገባ በወንጀል ድርጊቱ የሚደርሰውን ኪሳራ ይፋ ባደረገበት ሪፖርት አሳስቧል፡፡ እንደ ድርጅቱ መረጃ ከሆነ፤ በእስያ ምሥራቅ እና ደቡብ ምሥራቅ ብቻ በሣይበር በሚፈጸሙ ወንጀሎች ሳቢያ የ37 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ ደርሷል፡፡

ይህ ወንጀል ከእስያ አሕጉር ባሻገር ወደሌሎች አሕጉራት እየተዛመተ እንደሚገኝ የገለጸው ድርጅቱ፤ በሁሉም የዓለም ክፍል የሚገኙ ዜጎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡ በድርጅቱ የዕፅ እና ወንጀል ጉዳዮች ተቆጣጣሪ ጽሕፈት ቤት ሰኞ ባወጣው ሪፖርት፤ በተለይ በቻይና እና በደቡብ ምሥራቅ እስያ በሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች፤ በውንብድና የተደራጁ ቡድኖች በየዓመቱ በርካታ የሣይበር ወንጀሎችን በመፈጸም በአስር ቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር እንዲመዘበር ያደርጋሉ፡፡ የወንበዴ ቡድኖቹ የማጭበርበር ተግባሩን የሚፈጽሙት ሐሰተኛ የኢንቨስትመንት፣ የክሪፕቶከረንሲ እና ተዛማጅ ንገድ በማቅረብ ነው፡፡

በዋናነት የሚንቀሳቀሱት በምያንማር የድንበር አካባቢዎች እንዲሁም በካምቦዲያ እና ላኦስ ውስጥ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ በተዘጋጁ “ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች” ውስጥ ነው። ቡድኖቹ በአብዛኛው በሠራተኝነት የሚቀጥሯቸው በሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች አማካኝነት በቁጥጥር ስር የሚገቡ ግለሰቦችን ነው፡፡ የሚያሰማሯቸው ሠራተኞች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ማንኛውንም አገልግሎት እንዲሰጡ የሚገደዱ ናቸው፡፡

ሪፖርቱ የወንጀል ቡድኖቹ ከእስያ በተጨማሪ በአሁኑ ሰአት የወንጀል መረባቸውን ወደ ደቡብ አሜሪካ፣ አፍሪካ፣ መካከለኛው ምሥራቅ፣ አውሮፓ እና ፓሲፊክ እየዘረጉ እንደሚገኙ አመልክቷል፡፡ ከአፍሪካ አሕጉር ዛምቢያ፣ አንጎላ እና ናሚቢያ በወንጀለኞቹ ወጥመድ ውስጥ መግባታቸው ተጠቅሷል፡፡ ከፓሲፊክ ሀገሮች ውስጥ ፊጂ እና ቫኑዋቲ ተካተዋል፡፡

በሪፖርቱ መሠረት ቡድኖቹ ከደቡብ አሜሪካ የዕፅ አዘዋዋሪዎች፣ ከጣሊያን ማፊያዎች እና ከአየርላንድ ወንበዴ ቡድኖች ጋር በመተባበር የገንዘብ ማጭበርበሪያ ሥልት በመቀያየር በወንጀል ድርጊቱ ላይ ተሳትፎ ማድረግ ቀጥለዋል፡፡ የወንጀል ቡድኖች ተሰማርተዋል ከተባሉባቸው ሀገሮች መካከል በምያንማር ፖሊስ ባካሄደው ኦፕሬሽን ሰባት ሺሕ ሰዎችን ነጻ ማውጣት መቻሉን ሪፖርቱ አስታውሷል፡፡ ይህ ኦፕሬሽን በቻይና የታገዘ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ የወንጀል ቡድኖቹ መዳረሻቸውን በፍጥነት ስለሚቀያይሩ ለቁጥጥር አመቺ አለመሆኑን የገለጸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፤ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀማቸው የወንጀለኞቹን ዱካ እና የፋይናንስ ዝውውር ለመቃኘት የሚደረገውን ሥራ አስቸጋሪ እንዳደረገው አስታውቋል፡፡ ድርጅቱ እንደ ካንሠር ቀስ በቀስ እየተዛመተ ይገኛል ያለውን የወንጀል ድርጊት ለመጋፈጥ ሀገሮች በትብብር እንዲቆሙ ጥሪ አቅርቧል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular