Homeዜናና ወቅታዊዜናሳዑዲ ዐረቢያ የመጀመሪያዎቹን ሑጃጅ የምትቀበልበትን ቀን ይፋ አደረገች

ሳዑዲ ዐረቢያ የመጀመሪያዎቹን ሑጃጅ የምትቀበልበትን ቀን ይፋ አደረገች

የ1446 ዓ.ሂ መጀመሩን ይፋ ያደረገችው ሳዑዲ ዐረቢያ፤ የመጀመሪያዎቹን ሑጃጅ የምትቀበልበትን ቀን አሳውቃለች፡፡ የሀገሪቱ ሐጅ እና ዑምራ ሚኒስቴር፤ የመጀመሪያዎቹ ምዕመናን ቀጣይ ሣምንት ወደ ሀገሪቱ ይገባል ሲል ገልጿል፡፡

በዛሬው እለት ይፋ እንደተደረገው ከሆነ፤ ምዕመናኑ ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ የሚገቡት ሚያዝያ 21/2017 ነው፡፡

ሳዑዲ ዐረቢያ በቅዱሳኑ መካ እና መዲና ከተሞች፤ የሐጅ ወቅት በይፋ መጀመሩን ካስታወቀች በኋላ የዑምራን ጨምሮ ሌሎች ቪዛዎች ለምዕመናን እንዳይሰጥ እግድ ጥላለች፡፡ በዚህም ከመላው ዓለም ከ180 በላይ ሀገሮች የሚገቡ እንግዶችን ለመቀበል የሚደረገው ዝግጅት ተጠናቆ ከዚህ በኋላ ይገባሉ ተብሎ የሚጠበቀው የሐጅ ሥነ ሥርዐት የሚከውኑ ምዕመናን ብቻ ሆነዋል፡፡

የሀገሪቱ ባለስልጣናት ዜጎችም ሆኑ በሥራ ምክንያት ሳዑዲ ዐረቢያ ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም ግለሰብ፤ ከፊታችን ረቡዕ አንስቶ ወደ መካ ከተማ መግባት የሚፈልግ ከሆነ “አብሽር” አልያም “ሙቂም” በተሠኙ መተግበሪያዎች ቅድመ ምዝገባ ማካሄድ እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል፡፡

በመተግበሪያው ምዝገባ ሳያከናውኑ ለመግባት ሙከራ የሚያደርጉና ጊዜው ያለፈበት ፍቃድ የያዙ ላይ ቅጣት ሊጣልባቸው እንደሚችልም አስጠነቅቀዋል፡፡ በዚህም የፀጥታ አካላት የጂዳ መካ አውራ ጎዳናን እንዲሁም የጣኢፍ መካ መንገድን ጨምሮ በሁሉም ዋና ዋና የመዳረሻ መንገዶች ላይ ጥብቅ ፍተሻ ተግባራዊ ያደርጋሉ ተብሏል። እነዚህ ርምጃዎች የሚወሰዱት በቅድስቲቱ መካ ከተማ ከመላው ዓለም ለሐጅ ክንውን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ምዕመናን ሰስለሚጓዙ ሊፈጠር የሚችለውን መጨናነቅ ለመቀነስ ነው፡፡

የዘንድሮ ዓመት የሐጅ ሥነ ሥርዐት ክንውን ከግንቦት 27/2017 እስከ ሰኔ 2/2017 እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ በክንውኑ ከኢትዮጵያ ስድስት ሺሕ ምዕመናን ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ሑጃጅ በረራ ማድረግ የሚጀምሩት ግንቦት 6/2017 ሲሆን፣ የሚጠናቀቀው ግንቦት 30/2017 ነው፡፡

ባለፈው ዓመት ከመላው ዓለም ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ምዕመናን በሐጅ ሥነ ሥርዐት ላይ ተሳታፊ መሆናቸው ይታወሳል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular