የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፤ በዘንድሮ የሐጅ ሥነ ሥነ ሥርዐት ክንውን ላይ የሚሳተፉ ኢትዮጵያውያን በረራ የሚጀመርበትን ቀን ይፋ አድርጓል። በምክር ቤቱ የሐጅ እና ዑምራ ዘርፍ ይፋ በተደረገው መሠረት ምዕመናን በረራ የሚጀምሩት ግንቦት 6/2017 ይሆናል።
ጠቅላይ ምክር ቤቱ ይህን የገለጸው ዛሬ ሰኞ ሚያዝያ 13/2017 ነው። እንደ ምክር ቤቱ መረጃ ከሆነ፣ የኢትዮጵያውያን ሑጃጅ በረራ ግንቦት 6 ተጀምሮ ግንቦት 30/2017 ይጠናቀቃል።
በዚህ መረጃ ላይ ምክር ቤቱ የሑጃጅ በረራ የሚጀመርበትን ቀን ቢያሳውቅም በረራ የሚደረግበትን አየር መንገድ አልገለፀም። ምክር ቤቱ ባለፈው ዓመት የላካቸው 12 ሺሕ ምዕመናን የበረሩት በኢትዮጵያ አየር መንገድ እና በሳዑዲ ዐረቢያው ሳዑዲያ አየር መንገድ እንደነበር ይታወሳል። ከአየር መንገዶቹ መካከል የኢትዮጵያ አየር መንገድ 8 ሺሕ 500 በማስተናገድ ከፍተኛውን ቁጥር ወስዷል። በሳዑዲያ የበረሩት 3 ሺሕ 500 ኢትዮጵያውያን ነበሩ።
ጠቅላይ ምክር ቤቱ ምዝገባ ካከናወኑ ምዕመናን ውስጥ የአውሮፕላን ቲኬት በግል የሚቆርጡትንም ሲያስተናግድ ቆይቷል። የአየር ቲኬት በግል ቆርጠው ሐጅ የሚያደርጉ ምዕመናን መዳረሻ መዲና መሆኑን በመግለጽ፣ እስከ ሚያዚያ 14/2ዐ17 የተረጋገጠ የአውሮፕላን ቲኬት በተመዘገቡበት የሐጅ ምዝገባ ጣቢያ ይዘው በመቅረብ እንዲያስመዘግቡ አሳስቧል።
በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ የአየር ትኬታቸውን የማያስመዘግቡ እና መዳረሻቸውን ከመዲና ኤርፖርት ውጪ የሚያደርጉ የግል ትኬት ተጓዦች በሳዑዲ ዓረቢያ በሚኖራቸው ቆይታ ለሚደርስባቸው የአገልግሎት ክፍተት ኃላፊነቱን የሚወስዱ መሆኑን አሳውቋል።
በ1446 የዘንድሮ ሐጅ ላይ ከኢትዮጵያ የሚሳተፉ ምዕመናን ቁጥር ወደ ስድስት ሺሕ እንዲቀንስ መደረጉን የጠቅላይ ምክር ቤቱ ሐጅና ዑምራ ዘርፍ ባለፈው ሣምንት መጨረሻ ማሳወቁ ይታወሳል። ዘርፉ የተጠቀሰው ቁጥር ተሟልቶ ምዝገባ ስለመደረጉ ማረጋገጫ አልሰጠም። የሳዑዲ ዐረቢያ ሐጅ እና ዑምራ ሚኒስቴር ለምዝገባ ያስቀመጠው የጊዜ ሠሌዳ ሚያዝያ 10/2017 ተጠናቋል። (ሚንበር ቲቪ)












