የሳዑዲ ዐረቢያ ሐጅ እና ዑምራ ሚኒስቴር፤ ፍቃድ ያልያዙ ሑጃጅ ላይ እስራት እና የገንዘብ መቀጮ እንደሚጥል አስታወቀ፡፡ ሚኒስቴሩ ይህን ያስታወቀው፤ የ1446 ዓ.ሂ የሐጅ ሥነ ሥርዐት ክንውን መጀመሩን ይፋ ከተደረገ በኋላ ነው፡፡
ሚኒስቴሩ ይህን ባሳወቀበት መግለጫው፤ ፍቃድ ሳይኖራቸው ማጭበርበር ይፈጽማሉ ያላቸው ላይ ቅጣቱን የደነገገው፤ ቀድሞ ለሐጅ ክንውን ባስቀመጠው ደንብ መሠረት ለማስፈጸም መሆኑን ገልጿል፡፡ አዲስ ይፋ በተደረገው ደንብ በቅዱሳኑ ከተሞች ያለፍቃድ ከተገኙ ምዕመናን በተጨማሪ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ላይ ቅጣት ይጣልባቸዋል፡፡
በዚህም ያልተፈቀደላቸው የሐጅ ምዕመናንን የሚያጓጉዙ ላይ፤ ለእያንዳንዱ ጥሰት የ15 ቀናት እስራት ቅጣት እንዲጣል ተደንግጓል፡፡ በተጨማሪም በእያንዳንዱ ፍቃድ ያልያዘ ተሳፋሪ 10 ሺሕ የሳዑዲ ሪያል የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍሉ ይደረጋል፡፡ ተሳፋሪዎች በቁጥር ሲጨምሩ ቅጣቱም ከፍ የሚል ይሆናል፡፡
እንደዚህ ዓይነቱን ድርጊት በተደጋጋሚ እንዳይከሰት አጥፊዎች በአደባባይ እንዲታዩ ይደረጋል ያለው ሚኒስቴሩ፤ የፈጸሙት የውጭ ሀገራት ዜጎች ከሆኑ ቅጣት ካጠናቀቁ በኋላ ላልተወሰነ ጊዜ ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ ደግመው እንዳይገቡ እንደሚደረግ ገልጿል፡፡
የሳዑዲ ዐረቢያ መንግሥት ዘንድሮ ሐጅ ማከናወን የሚችሉት ሕጋዊ ቪዛ የሚይዙ ብቻ እንደሆኑ ምዕመናን በድጋሚ እንዲያውቁት ሲል አሳስቧል፡፡ የሐሰት ሠነድ በመጠቀም የተያዘ ማንኛውም ሰው በሕጉ መሠረት በቁጥጥር ስር ውሎ ለፍርድ እንደሚቀርብ በማስታወስ፤ ለዑምራ ክንውንም ሆነ ሌሎች የቪዛ ዐይነቶችን መስጠት ማቆሙንም ከዚህ ቀደም አሳውቋል፡፡
ባለፈው ዓመት በሐጅ ሥነ ሥርአት ክንውን ላይ ከመላው ዓለም ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ምዕመናን ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ በወቅቱ ከ1 ሺህ 300 በላይ የሚሆኑት ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ለኅልፈት ሰበብ ሆኗል የተባለው የተመዘገው ከፍተኛ የሙቀት መጠን ያስከተለው ንዳድ የተባለ ቢሆንም፤ የሳዑዲ ዐረቢያ ባለሥልጣናት ሕጋዊ ሠነድ ያልያዙ ምዕመናንን ለተፈጠረው መተፋፈግ ተጠያቂ አድርገዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












