Homeዜናና ወቅታዊዜናልዩ ዘገባ፡ ትምሕርት ሳይከታተሉ “ለብሔራዊ ፈተና የሚቀመጡት” የአክሱም ሙስሊም ሴት ተማሪዎች

ልዩ ዘገባ፡ ትምሕርት ሳይከታተሉ “ለብሔራዊ ፈተና የሚቀመጡት” የአክሱም ሙስሊም ሴት ተማሪዎች

በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ ሴት ተማሪዎች በትምህርት ቤቶች በተጣለው ሒጃብ ክልከላ ምክንያት፤ ከታኅሣሥ 8/2017 አንስቶ ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነው ቆይተዋል፡፡ ተማሪዎቹ ከትምህርት ቤቶቹ ርእሰ መምሕራን ጀምሮ፣ ለአክሱም እስልምና ጉዳዮች እና ትምህርት ቢሮ በጉዳዩ ላይ ቅሬታ ቢያቀርቡም አሁንም ድረስ መፍትሔ ሊያገኙ አለመቻላቸውን ለ“ሚንበር ቲቪ” ተናግረዋል፡፡ ይህንኑ የተማሪ ወላጆችም አረጋግጠዋል፡፡

የተማሪዎቹን ጉዳይ በተመለከተ የአክሱም ወረዳ እስልምና ጉዳዮች፣ የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች እንዲሁም የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮ ጠቅላይ ምክር ቤት፤ በተለያዩ ጊዜያት በሰጧቸው መግለጫዎች ድርጊቱን በማውገዝ የተማሪዎቹን መመለስ ሲወተውቱ ነበር፡፡ የወረዳው እስልምና ጉዳዮች ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ፤ የትምህርት ቤቶቹ ውሳኔ ላይ እግድ ቢጣልም ተፈጻሚ ሳይሆን ቀርቷል፡፡

ይህንኑ ተከትሎ በትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አስተባባሪነት፤ ጥር 13/2017 በመቐለ ከተማ ሠልፍ እንደተካሄደ ይታወሳል፡፡ ሠልፉ የተከናወነው “ሒጃቧንም ትለብሳለች ትምህርቷንም ትማራለች” በሚል መሪ ቃል ነበር፡፡ በሠልፉ ከመቐለ እና አካባቢው በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በመሳተፍ ድምጽ አሰምተዋል፡፡ በዚሁ እለት የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ተወካዮች ለቀድሞው የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ጉዳዩ እልባት እንዲሰጠው ጠይቀዋል፡፡ የተወካዮቹ ጥያቄም ሆነ ሠልፉ ተማሪዎቹን ወደ ትምህርት ገበታ መመለስ ሳይችል ቀርቷል፡፡

ይህ በእንዲህ ባለበት ሌላው አነጋጋሪ የነበረው ለብሔራዊ ፈተና የሚቀመጡ ተማሪዎች በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ላይ ለመቀመጥ ቅጽ እንዲሞሉ አለመደረጉ ነበር፡፡ ተማሪዎች ቅጽ የሚሞሉበት የጊዜ ሠሌዳ ከሦስት ወራት በፊት ታኅሣሥ 30/2017 ተጠናቋል፡፡

ጉዳዩ እልባት ሳያገኝ እስካሁን ድረስ ዘልቋል በሚል ሁለት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የትምህርት ሚኒስቴር ማክሰኞ ሚያዝያ 7/2017 በሕዝብ ተወካዮ ምክር ቤት የ2017 በጀት ዓመት የ9 ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረበበት ወቅት ጥያቄ አንስተዋል፡፡ ጥያቄውን ያቀረቡ ሁለት የምክር ቤት አባላት፤ አክሱምን ጨምሮ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች በሒጃብ ምክንያት ከትምህርት ገበታ ቢደረግም የትምህርት ሚኒስቴር መፍትሔ አለመስጠቱን ተናግረዋል፡፡ ተወካዮቹ የሴት ተማሪዎችን ሒጃብ እና ኒቃብ ጉዳይ መፍትሔ እንዲሰጠውም ጠይቀዋል፡፡

ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)፤ በትግራይ ክልል ስለሚገኙ ተማሪዎች “ምንም አላደረጋችሁም” መባላችን “ትክክል አይደለም” ሲሉ የሚመሩት መስሪያ ቤት አድርጓል ያሉትን በመጥቀስ ተከላክለዋል፡፡ እንደ ብርሃኑ (ፕ/ር) ከሆነ፤ ለ12ኛ ክፍል ፈተና የሚቀመጡ ተማሪዎች ጉዳዩ በተሰማበት ቀን፤ በተማሪዎች ምዘና ኤጀንሲ አማካኝነት እንዲመዘግቡ (ቅጽ እንዲሞሉ) ተደርገዋል፡፡ የተማሪዎቹን ቅጽ መሙላቱን በተመለከተ ሚንበር ቲቪ ዛሬ ሐሙስ ሚያዝያ 9/2017 ያናገራቸው ተማሪዎች እና ወላጆች፤ ቅጹ መሞላቱን ቢያረጋግጡም፤ እንዲሞሉ የተደረገው ከትምህርት ቤት ቅጽር ግቢ ውጪ የጊዜ ሰሌዳው ካለፈ በኋላ በጥር ወር ነው፡፡  

ሆኖም ተማሪዎቹ ቅጹን ቢሞሉም አሁንም ድረስ ተመልሰው ትምህርት እየተከታተሉ ባለመሆኑ፤ ለፈተና “መቀመጥ አልያም አለመቀመጣቸውን ርግጠኛ መሆን እንዳልቻሉ” ሥሟ እንዲጠቀስ ያልፈለገች የ12ኛ ክፍል ተማሪ ለሚንበር ቲቪ ተናግራለች፡፡ በአሁኑ ሰዓት ተማሪዎች ለፈተና የሚቀመጡ ከሆነም በቤት ውስጥ በግል ከሚያደርጉት ጥናት ውጪ እያገዛቸው የሚገኝ አካል አለመኖሩንም አስረድታለች፡፡ በተማሪዋ የተነሳው ወደ ትምህርት ገበታ የመመለስ እንዲሁም ለፈተና መቀመጥ አልያም አለመቀመጥ የትምህርት ሚኒስትሩ በምክር ቤት ማብራሪያ አልሰጡበትም፡፡

ከዚሁ ጋር በተገናኘ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውይይት ርእሰ ጉዳይ የነበረው፤ የሒጃብ እና ኒቃብ ዘላቂ መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል የሚለውን የተመለከተው ነው፡፡ በዚህ ላይ በተመሳሳይ ማብራሪያ የሰጡት የትምህርት ሚኒስትሩ፤ “በሒጃብ ምክንያት ማንም ትምህርት ቤት መከልከል አይችልም” ሲሉ አስረግጠው ቢናገሩም፤ “ኒቃብ ግን የተለየ” ነው ብለዋል፡፡ የኒቃብን ጉዳይ የተለየ ነው ለማለታቸው “ልጆች ባሉበት ትምህርት ቤት የአንድ ሰው ፊት ተሸፍኖ በሚገባ ጊዜ የደኅንነት ሥጋት አለው” የሚል መከራከሪያ አቅርበዋል፡፡

ጥያቄውን ላቀረቡት አንደኛው የምክር ቤት አባል ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ፤ “[እርስዎ ባሉበት] ከመጅሊስ ሰዎች ጋር ተሰብስበን ተነጋግረን ተማምነናል” ሲሉ አስረድተዋል፡፡ አክለውም “በኒቃብ ላይ ሕግ ማስቀየር ፓርላማ አምጥታችሁ ማስቀየር የምትችሉ ከሆነ ማስቀየር ነው እንጂ፤ በየጊዜው ርእሰ ጉዳይ እየሆነ የግጭት ምንጭ መሆን የለበትም” ሲሉ ጉዳዩ በእርሳቸው በኩል መፍትሔ የሚሰጠው እንዳልሆነ ጠቁመዋል፡፡ ሚኒስትሩ በዚሁ ንግግር ከመጅሊስ ሰዎች ጋር “ተማምነናል” ያሉበት ንግግር መቼ እንደተደረገ ቀኑን አልጠቀሱም፡፡ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር “መተማመን ላይ” ስለመደረሱ ከዚህ ቀደም የገለጸው ነገር የለም፡፡

በአንጻሩ በስሩ የሚገኘው የዑለማ ምክር ቤት “ሰላትንና ሒጃብን” አስመልክቶ ታኅሣሥ 23/2017 በሰጠው ፈትዋ፤ “ማንኛዋም ሙስሊም ሴት በማንኛውም ቦታና ሁኔታ እስላማዊ አለባበስን የመጠበቅ ግዴታ አለባት” ያለ ሲሆን፣ “ማንኛውም አካል ወይም ግለሰብ ይህንን የፈጣሪን ግዴታ (ትዕዛዝ) መከልከልም ሆነ ማደናቀፍ እንደሌለበት” አሳስቧል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular