Homeዜናና ወቅታዊሰሞነኛ ጉዳዮችየ1446 ዓ.ሂ ሐጅ በይፋ ተጀመረ

የ1446 ዓ.ሂ ሐጅ በይፋ ተጀመረ

ሳዑዲ ዐረቢያ በቅዱሳኑ መካ እና መዲና ከተሞች፤ የሐጅ ወቅት በይፋ መጀመሩን አስታውቃለች፡፡ የሀገሪቱ ሐጅ እና ዑምራ ሚኒስቴር ይህን የገለጸው፤ ለዑምራ ወደ ሀገሪቱ የሚገቡ ምዕመናንን ከእሑድ አንስቶ እንዲቆሙ ካደረገ በኋላ ነው፡፡ በዚህም ከመላው ዓለም ከ180 በላይ ሀገሮች የሚገቡ እንግዶችን ለመቀበል የሚደረገው ዝግጅት ተጠናቆ ከዚህ በኋላ የሚገቡት የሐጅ ሥነ ሥርዐት የሚከውኑ ምዕመናን ብቻ ይሆናሉ፡፡

በሚኒስቴር መረጃ መሠረት የሳዑዲ ባለሥልጣናት ለ3 ሚሊዮን ሑጃጅ፤ “ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ምቹ አገልግሎት ለማቅረብ” ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ በመስጂድ አንነበዊ እና መስጂደል ሐረም በተደረገው የማስፋፊያ ግንባታ የማስተናገድ አቅማቸውን በ25 በመቶ ማሳደግ ተችሏል፡፡ በሚና፣ በአረፋት እና በሙዝደሊፋ የሚገኙ ጊዜያዊ መጠለያዎችን አቅም በማሳደግ የጂፒኤስ መከታተያ እና የአየር ማቀዝቀዣ እንዲገጠም ተደርጓል፡፡ አደጋዎችን ለመከላከል 10 ሺሕ የደኅንነት ሠራተኞች፣ 500 የሕክምና ቡድኖች እና ሁለት ሺሕ አምቡላንሶች ዝግጁ መደረጋቸውን ኢስላሚክ ኢንፎርሜሽን ዘግቧል።

የሳዑዲ ዐረቢያ ብሔራዊ ሜትሮሎጂ ማዕከል እንዳሳወቀው፤ የዘንድሮው የሐጅ ሥነ ሥርዐት እንደ አምናው ሁሉ በከፍተኛ የበጋ ሙቀት ውስጥ የሚደረግ ቢሆንም በቅርብ ዓመታት የመጨረሻው ይሆናል፡፡ በቀጣዩ ዓመት የጊዜው ዑደት ወደ ፀደይ ወራት ይሻገራል፡፡ በፀደይ ወራት የሚከወነው የሐጅ ሥነ ሥርዐት ለሚቀጥሉት 16 ዓመታት የሚቆይ ነው፡፡ በቀጣይ ዓመታት የሙቀቱ መጠኑ ይቀንሳል፡፡ ባለፈው ዓመት ከተሳተፉ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ምዕመናን መካከል 1 ሺሕ 300 የሚሆኑት በወቅቱ በተመዘገው ከፍተኛ ሙቀት ምክንያት ሕይወታቸው ማለፉ ይታወሳል፡፡

ከኢትዮጵያ ለሐጅ ክንውን በወቅቱ ከተጓዙ ኢትዮጵያውያን ውስጥ በሙቀት ሳቢያ ሕይወቱ ያለፈ ምዕመን አልተመዘገበም፡፡ ወደ ሀገሪቱ ከተጓዙት 12 ሺሕ ኢትዮጵያውያን ምዕመናን ውስጥ በሙቀቱ ሳቢያ ለኅልፈት የተዳረገ ባይኖርም በሌላ ምክንያት አምስት ሰዎች ሞተዋል፡፡ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ዘንድሮ 10 ሺሕ ምዕመናን ይሳተፋሉ በሚል ምዝገባ የጀመረ ቢሆንም፤ እስካሁን ድረስ የታቀደው ቁጥር መሙላት አልያም አለመሙላቱን አላሳወቀም፡፡  

በሌላ መረጃ፤ የሳዑዲ ዐረቢያ ሐጅ እና ዑምራ ሚኒስቴር በመዲና የሚገኘውን ረውዳውን የሚዘይሩ ምዕመናን ዕለታዊ ቁጥር ከ52 ሺሕ በላይ እንዲሆን ውሳኔ ማሳለፉን ገልጿል፡፡ ይህ ውሳኔ ይፋ የተደረገው በዛሬው እለት ነው፡፡ በምዕመናን የሚናፈቀው ረውዳ፤ በነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) መስጂድ ሚንበር እና በመኖሪያ ቤታቸው መሃል የሚገኝ ሥፍራ ነው፡፡ 330 ስኩዌር ሜትር የሚሸፍነው ሥፍራው፣ በአንድ ሰዓት ውስጥ 800 ምዕመናንን ሲያስተናገድ ቆይቷል፡፡ በመልዕክተኛው “የጀነት ጨፌ” በሚል የተመሠከረለትን ረውዳውን ለመዘየር የታደለ ምዕመን በሥፍራው የሚቆይበት ጊዜ በሰዓት የተገደበ ነው፡፡ በዚህም አንድ ምዕመን መቆየት የሚፈቀድለት የጊዜ ርዝማኔ ቢበዛ ሠላሳ ደቂቃ ብቻ ነው፡፡ በዘንድሮው የሐጅ ሥነ ሥርዐት ክንውን ወቅት ረውዳውን ለመዘየር የሚፈልጉ ምዕመናን፣ በሥፍራው ለመገኘት “ኑሱክ” በተሰኘው የሑጃጅ መተግበሪያ ቀጠሮ ማስያዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular