በአዲስ አበባ ሜክሲኮ አካባቢ የሚገኘው የተባረክ መስጂድ ማስፋፊያ አጥር ቅዳሜ ሚያዝያ 4/2017 እኩለ ሌሊት በፀጥታ አካላት እንዲፈርስ ተደርጓል፡፡ የአጥሩን መፍረስ ተከትሎ የከተማው እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት እሑድ ሚያዝያ 5/2017 ማለዳ ድርጊቱን ተቃውሞ መግለጫ አውጥቷል፡፡ ከ“ሚንበር ቲቪ” ጋር የስልክ ቆይታ ያደረጉት የምክር ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሪያድ ጀማል፤ የፈረሰው አጥር ወደ ቀድሞው ሁኔታው ተመልሶ እንዲገነባ ጠይቀዋል፡፡ ይህ ሳይፈጸም ምንም ዐይነት ንግግር እንደማይጀመርም ገልጸዋል፡፡
ይሁን እንጂ የክፍለ ከተማ አስተዳደር በተመሣሣይ በሌሊት ባወጣው መግለጫ፤ የመስጂዱ አጥር እንዲፈርስ የተደረገው “መንግሥት ውሳኔ ያልሰጠበት መሬትን ያለአግባብ ከሕግ ውጪ ለመያዝ የተደረገ ተግባራዊ እንቅስቃሴን ለመከላከልና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ” ነው ብሏል፡፡ ክፍለ ከተማው ሥፍራውን “ያለምንም ሕጋዊ ፍቃድ የመስጂዱ እንደሆነ በማስመሰል በመንግሥት የታጠረውን ቦታ የመስጂዱን ታፔላ እና በር በመሥራት የመስጂዱ አካል በማስመስል ሕገ ወጥ ተግባር” ነው ብሎታል፡፡
የቂርቆስ ክፍለ ከተማ መጅሊስ በአንጻሩ ክፍለ ከተማው “ሕገ ወጥ” ነው ላለው ተግባር፤ ሰኞ ሚያዝያ 6/2017 ምላሽ ሰጥቷል፡፡ በዚህ ምላሽ ላይ የመስጂዱን ማስፋፈፊያ በተመለከተ የነበሩ ሒደቶችን ዘርዝሯል፡፡ ከተጠቀሱት መካከል ተከታዮቹ አስር ነጥቦች ተካተዋል፡-
- መስጂዱ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለመገንባት ኢስላማዊ ዩኒቨርሲቲ፣ የማኅበረሰብ አቀፍ የድጋፍ ማእከል እና ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ ተቋማትን ለመገንባት ዲዛይን በማሠራት ለአዲስ አበባ ከተማ መሬት አስተዳደር ጥያቄ በማቅረብ ከሁለት ዓመት በላይ ቢጠበቅም በጊዜው ምላሽ አላገኘም
- ከአንድ ዓመት ወዲህ በድጋሚ ለከተማው መሬት አስተዳደር ዲዛይኑን በማስደገፍ የፕላን ስምምነት ሲጠየቅ፤ “ቦታው ሙሉ ለሙሉ ለሪል እስቴት አልሚዎች የተሰጠ መሆኑን እና በፕላኑ መሠረት ቦታው ላይ መስጂዱ እንደሌለ” ለመስጂዱ ስለተገለጸ፤ ካርታውን በማቅረብ ክርክር በማድረግ “ከብዙ ምልልስ እና ክትትል በኋላ” መስጂዱ ከ50 ዓመታት በላይ ቦታው ላይ እንደቆየ በተደረገው ክትትልና ማጣራት ተረጋግጧል፡፡ መስጂዱ “ካርታ እያለው ሌላ ካርታ መደረቡ አግባብነት የጎደለው አካሄድ መሆኑ” ላይ መተማመን ተደርሷል
- በዚህ መሐል ላይ የሪል እስቴት አልሚዎች የመስጂዱ ይዞታ በግልፅ ተለይቶ ያልተነገራቸው በመሆኑ ሥራቸውን መቀጠል እንዳልቻሉ በመግለጽ፤ ከመስጂዱ አስተዳደር ጋር ውይይት እንዲጀመርላቸው በመጠየቃቸው በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ የሜጋ ፕሮጀክት ተወካይን ጨምሮ ከአልሚው ኤግል ሂልስ ሪል እስቴት፣ ከክፍለ ከተማው መጅሊስ፣ ከክፍለ ከተማው የወረዳ 10 መጅሊስ፣ ከክፍለ ከተማው የወረዳ 10 መሬት አስተዳደር፣ የወረዳ 10 ደንብ ማስከበር እና ሌሎችም ጋር ውይይት ተካሄዷል
- በዚህ ውይይት የመስጂዱን ወሰን የመስጂዱ አስተዳደር ኮሚቴ እና የወረዳ 10 መሬት አስተዳደርና ደንብ ጽ/ቤት ተወካዮች ቦታውን በማመላከት፤ የቀረው ቦታ ላይ የሪል እስቴቱ ግንባታውን ለመጀመር እንዲስችላው “የመስጂዱ ቦታ ነው ተብሎ በሁለቱም አካላት የታመነበትን ቦታ” መስጂዱ በራሱ ወጪ እንዲያጥር ስምምነት ተደርጓል፡፡ ነገር ግን በወቅቱ ከአዲስ አበባ መጅሊስ ጋር በጉዳይ ላይ ውይይት ለማድረግ ጊዜ በመፍጀቱ ምክንያት የሪል እስቴቱ ተወካዮች “የዚህን ያህል ጊዜ ለመጠበቅ ጊዜ እንደሌላቸው በመግለፅ” የሚታጠረው አጥር የመስጂዱንና የሪል እስቴት የድንበር መለያ በመሆኑ ምክንያት “በራሳቸው ወጪ ሊያጥሩት በመወሰናቸው” ሥራው ተሠርቷል፡፡ ዙሪያው ታጥሮ ሲጠናቀቅ የመውጫ መግቢያው ሙሉ በሙሉ በብረት በር ተገጥሟል

- ከተጠናቀቀ ሳምንት ካለፈ በኋላ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ አስተዳደር አጥሩ ከእውቅናችን ውጪ ተሠርቷል በሚል የመስጂዱን አስተዳደር በማናገር ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡ ሆኖም የክፍለ ከተማው አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈፃሚ በጉዳዩ ላይ መነጋገር አለብን በማለት ጥሪ በማቅረባቸው የቂርቆስ ክፍለ ከተማ አስተዳደር እንዲሁም የወረዳ 10 ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ የብልፅግና ፓርቲ ኃላፊ፣ ሥራ አስፈጻሚ ቢሮ ኃላፊ፣ ሰላምና ጸጥታ ኃላፊ፣ ደንብ ማስከበር ጽ/ቤት ኃላፊ፣ የመሬት አስተዳደርና የመጅሊስ እና ኢማሙን ጨምሮ መስጂዱ ተወካዮች የተሳተፉበት 4 ሰዓት የፈጀ ውይይት ተካሔዷል
- በውይይቱ ላይ መግባባት ላይ ያልተደረሰባቸው ጉዳዮች ላይ “በቀጣይ ለመነጋገር” ተለዋጭ ቀጠሮ የተያዘ ቢሆንም የከተማው አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር ሌላ ጥሪ በማቅረቡ ከሰላምና ጸጥታ ቢሮ፣ ከከተማው አስተዳደር ቢሮ፣ የአዲስ አበባ እና ቂርቆስ ክፍለ ከተማ መጅሊስ ሥራ አስፈፃሚ አባላትና ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የተባረክ መስጂድ ኢማም ባሉበት ውይይት ተደርጓል
- በውይይቱ ላይ “በመስጂዱ ቅጥር ጊቢ ውስጥ የአጥር ዙሪያ ግንባታ በመንግሥት የታችኛው መዋቅር በቀረበው ሪፖርት መሠረት ያለመሆኑን በማመን” በቀጣይ በታችኛው መዋቅር “ተዛብቶ በቀረበው ሪፖርት ላይ” ግምገማ እንደሚቀጥል ገልጸዋል
- አሁን መስጂዱ ውስጥ የተገነባውና የተሠራው ሥራ በሙሉ ባለበት እንዲቆይ እና መስጂዱም አለኝ የሚለውን ዶክመንት ይዞ ጥያቄውን እንዲቀጥል እስከዚያ ድረስ ግን ምንም ዐይነት ተጨማሪ ሥራ እንዳይሠራ ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ቀጣዩ ውይይት ረመዳን እንደወጣ እንደሚሆንም የስምምነቱ አካል ነበር፡፡
- ረመዳን 28 የተባረክ መስጂድ ባዘጋጀው የኢፍጣር መርሐ ግብር ላይ ተጋባዥ ከነበሩት እንግዶቹ መካከል የቂርቆስ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር አዲሱ ሻንቆ በፕሮግራሙ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ አንዳንድ ግለሰቦች በዚህ መስጂድ የተደረገውን ግንባታ ይፈርሳል ብለው የሚሉት አሉባልታ እንደሆነና ሁሉም ነገር በውይይት እና “በድርድር እየተሠራ ያለ መሆኑን” ገልጸዋል፡፡ የመስጂዱ የወደፊት ፕላንና እቅድ በከተማ መስተዳደሩ የሚመለስ ስለሆነ አሁን ከተሠራው ውጭ ሌላ ምንም ነገር ባለመሥራት ጥያቄያችሁ መልስ እስኪያገኝ ከከተማውና ከክፍለ ከተማው አስተዳደር ጋር ለልማቱ በጋራ እንድትሰለፉ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል
- የመስጂዱ ጉዳይ በዚህ መልኩ ክትትል እየተደረገ በመቆየት መጋቢት 25/2017 የአዲስ አበባ መሬት አስተዳደር መስጂዱ አሁን በታጠረበት ልክ ባለሞያዎችን በመላክ ልኬት ወስዷል (ሚንበር ቲቪ)












