የኳታር እና የግብፅ መሪዎች ፍልስጤማውያንን ከቀዬ የማፈናቀል ዕቅድ ሙሉ በሙሉ እንደሚቃወሙ በድጋሚ ያረጋገጡት፤ በዶሐ ባደረጉት ውይይት ነው፡፡ ውይይቱ የተደረገው በኳታር አሚር ሸይኽ ተሚም ቢን ሐማድ አስሳኒ እና በግብጹ ፕሬዝዳንት ዓብዱልፈታህ አል ሲሲ መካከል ነው፡፡
ሁለቱ መሪዎች በተገናኙበት ወቅት በሐማስ እና በእስራኤል መካከል የተደረሰውን የተኩስ አቁም እንዲሁም የምርኮኞች ልውውጥ በድጋሚ ለማስጀመር እየተደረጉ ስለሚገኙ የቅርብ ጊዜ ጥረቶች ማንሳታቸውን አናዶሉ ኤጀንሲ የግብጽ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤትን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል፡፡ እንደ ዘገባው፤ አልሲሲ እና ተማም ቢን ሐማድ፤ በጋዛ ውስጥ ተባብሷል ያሉትን የሰብዓዊ ቀውስ ሁኔታና በጋዛ ውስጥ ለሚገኙ ፍልስጤማውያን በቂ ርዳታ በሚደርስበት መንገድ ላይ ተነጋግረዋል፡፡
በጋዛ የሰብዓዊ ርዳታ መዳረሻዎች በእስራኤል ወታደሮች እንዲዘጉ ከተደረገ 45 ቀናት ተቆጥረዋል፡፡ ወታደሮቹ ከርዳታው በተጨማሪ የሚሰነዝሩትን ጥቃት በመቀጠል ባለፈው አንድ ዓመት ከመንፈቅ ሕይወታቸው የተቀጠፈ ፍልስጤማውያን ቁጥር ከ51 ሺሕ ተሻግሯል፡፡
ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት፤ ከአምስት ወራት በፊት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር ዮቭ ጋላንት በጋዛ በፈጸሙት የጦር እና በሰብዓዊነት ላይ በፈጸሙት ወንጀል የእስር ማዘዣ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡ እስራኤልም በአጎራባች ግዛት ላይ በከፈተችው ጦርነት ምክንያት በዓለም አቀፉ የፍትሕ ፍርድ ቤት የዘር ማጥፋት ክስ ቀርቦባታል። (ሚንበር ቲቪ)












