የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን፤ በአዲስ አበባ ከተማ በእስላማዊ የካፒታል ገበያ ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት አካሔዷል። በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ የተካሔደው አውደ ጥናት ለሦስት ቀናት የቆየ ነበር።
አውደ ጥናቱ የተዘጋጀው የእስላማዊ ፋይናንስ ማማከር አገልግሎት ላይ በተሰማራው ኢስላሚክ ፋይናንስ አድቫይዘሪ ኤንድ አሹራንስ ሰርቪስስ (IFASS)፣ በኤፍ.ኤስ.ዲ ኢትዮጵያ እና በተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ኢትዮጵያ ድጋፍ መሆኑን የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ገልጿል። በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ማዕቀፍ ውስጥ በእስላማዊ ፋይናንስ የወደፊት የልማት ዕቅድ እንዲሁም በተዘጋጀው ፍኖተ ካርታ ላይ ማብራሪያ ቀርቧል።
ፖሊሲ አውጪዎችን፣ ተቆጣጣሪ አካላትን እና የሃይማኖት መሪዎችን ባሳተፈው የመጀመሪያ ቀን ውሎ፣ በኢትዮጵያ እስላማዊ የፋይናንስ ምርቶች ማስተዋወቅ እና ትግበራ ላይ ውይይት ተደርጓል። ኢስላሚክ ፋይናንስ አድቫይዘሪ ኤንድ አሹራንስ ሰርቪስስ፤ ለኢትዮጵያ ባዘጋጀው የእስላማዊ ካፒታል ገበያ ፍኖተ ካርታ ውይይት የተደረገው በዚህ ወቅት ነው።

በሁለተኛው ቀን የተደረገው ውይይት ትኩረቱን ያደረገው በተቋማዊ ዝግጁነት እና የቁጥጥር ጉዳዮች ላይ እንደነበር ተገልጿል። በመጨረሻ ቀን ከግል ዘርፍ ባለድርሻ አካላት በቀረበው ፍኖተ ካርታ ላይ የተሰጡ አስተያየቶች ተሰብስበዋል።
የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን፤ በሀገሪቱ የእስላማዊ የካፒታል ገበያን ለማስተዋወቅ አስፈላጊ የሆነውን የቁጥጥር ማዕቀፍ ለማዘጋጀት እንቅስቃሴ መጀመሩን ይፋ ያደረገው በተያዘው ዓመት ኅዳር ወር መገባደጃ ነበር። በኤፍ.ኤስ.ዲ ኢትዮጵያ እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም የሚደገፈው ፕሮጀክት፤ አምስት ወራት የሚፈጅ መሆኑ በወቅቱ ተገልጿል።
ከዚሁ ጋር በተገናኘ በሀገሪቱ የካፒታል ገበያ ሥራ ላይ ብቻ የተሰማሩት የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ ሲቢኢ ካፒታል እና የወጋገን ባንኩ ወጋገን ካፒታል ፍቃድ ማግኘታቸው ባለፈው መጋቢት ወር ይፋ ተደርጓል። በተጨማሪም አምስት የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጭዎች በወቅቱ ፍቃድ አግኝተዋል።
ከኢንቨስትመንት ባንኮቹ መካከል ሲቢኢ ካፒታል፤ የሀገሪቱን የተለያዩ የኢንቨስትመንት ፍላጎቶች ለመደገፍ ሸሪዓን መሠረት ያደረገ አሠራር ለማካተት በዕቅድ መያዙን ገልጿል።
እስላማዊ ካፒታል ገበያ የሰፊው የካፒታል ገበያ ንዑስ ዘርፍ መሆኑ ይታወቃል። በገበያው ሸሪዓን የሚያሟሉ ሠነደ ሙዓለ ንዋዮችና የኢንቨስትመንት አማራጮች ይቀርባሉ። (ሚንበር ቲቪ)












