ለምሥራቅ አፍሪካዋ ሀገር ሩዋንዳ እና ሩዋንዳዊያን፤ ከዛሬ መጋቢት 29 (ኤፕሪል 7) ጀምሮ ያሉት ቀጣይ 100 ቀናት ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው ናቸው። እነዚህ ቀናት በልዩ ሁኔታ ሲታሰቡ ዘንድሮ 31 ዓመት ደፈነ። የሀገሬው ሰዎች ዕለቱን “ኩዊቡካህ” ሲሉ ሠይመውታል። “ለማስታወስ/አስታውስ” ተብሎ ወደ አማርኛ ሊመለስ ይችላል። በዚህ ቀን የሚያስታውሱት እ.አ.አ በ1994 የተከሰተውን “ጨለማ” ሲሉ የሚጠሩትን የሀገራቸውን የጎደፈ ታሪክ ነው። ያን ጊዜ ሩዋንዳዊያን በዘር ተቧድነው ሲፋጁ ከራሳቸው አንድ ሚሊዮን ገደማ ነፍስ አጉድለዋል። በወቅቱ “ቱትሲ” ተብለው በሚጠሩ ጎሳዎች ላይ የተፈጸመውን የዘር ፍጅት ለማስታወስ፤ ዕለቱን፣ ሣምንቱን እና ወራቱን ጭምር ይገለገሉበታል። የተለያዩ ተግባራትን እየከወኑ ሕይወታቸውን ላጡት መታወሻ፤ ለተረፉት ደግሞ ክብር ለመስጠት ይሰበሰባሉ።
ሩዋንዳዊያኑ ይህን ሲያደርጉ በአብሮነት ከጎን የሚቆሙ አሉ። የአፍሪካ ኅብረት አንደኛው ነው። ዛሬ በቅጽር ግቢው ማንዴላ አዳራሽ የዘር ፍጅቱን ለማሰብ ፕሮግራም አዘጋጅቶ ነበር። ነገር ግን በዚህ ስብሰባ ላይ ከተለያዩ አፍሪካ ሀገሮች ተወካዮች ጋር በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር መገኘታቸው ያተጠበቀ ክስተት ነበር። በዚህም በርካታ ተወካዮች አምባሳደሩ ሥፍራውን ለቀው እንዲወጡ መጠየቃቸውን ሚድል ኢስት ዐይ ዘግቧል። ሰውዬው በተወካዮቹ ቅሬታ ተገደው ከአዳራሹ እንዲወጡ ተደርጓል። እንደ ዘገባው ከሆነ፤ ተቃውሞው የመጣው አምባሳደሩ የተወከሉባት እስራኤል በጋዛ እየፈፀመች ከምትገኘው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከዘር ፍጅት ጋር የሚተካከል ነው ከተባለው ወንጀል ጋር በተገናኘ ነው።
የአፍሪካ ኅብረት አባል ሀገሮች ተወካዮች በሥፍራው “ከአምባሳደሩ ጋር በአንድ አዳራሽ ለመሰብሰብ እንቸገራለን፤ ይውጡልን” የሚል ጥያቄ ካቀረቡ በኋላ፣ ሰውዬው እስኪሸኙ ድረስ ስብሰባው ተቋርጦ መቆየቱንም ሌላኛው የዜና ምንጭ ሚድል ኢስት ሞኒተር ዘግቧል። አምባሳደሩ በማን ጋባዥነት ወደ አዳራሹ እንደመጡ እንደሚያጣራ የገለጸው ኮሚሽኑ፤ ከዚህ ቀደም በተመሣሣይ ሌላ የእስራኤል ተወካይ ከአዳራሹ ማሰናበቱን ዘገባዎቹ አስታውሰዋል። (ሚንበር ቲቪ)












