ፈረንሣይ ከሳዑዲ ዐረቢያ ጋር የፍልስጤም እና እስራኤልን ግጭት ያስቀራል ባሉት የሁለት ሀገሮች ምሥረታ የመፍትሔ አማራጭ ላይ የሚመክር ኮንፍረንስ ሊያዘጋጁ መሆኑን የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ተናገሩ፡፡ ማክሮን በዐረብ ሊግ የጸደቀውን የጋዛ መልሶ ግንባታ ዕቅድ እንደሚደግፉ ገልጸዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ይህን የተናገሩት በግብጽ ካይሮ በተገኙበት ወቅት ነው፡፡ ከሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዓብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የፍልስጤም እና እስራኤል ግጭት “ዘላቂ ፖለቲካዊ መፍትሔ” ሊበጅለት ይገባል ብለዋል፡፡ ኮንፍረንሱ ግብጽን ጨምሮ በቀጣናው ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር የሚዘጋጅ እንደሚሆንም ገልጸዋል፡፡
በጋዛ እና በመካከለኛው ምሥራቅ ቀጣና መረጋጋትን እና የሕዝቦችን ደኅንነት የሚረጋግጠው “ፖለቲካዊ ምላሽ መስጠት ብቻ” መሆኑን በመጥቀስ፤ ከሳዑዲ ዐረቢያ ጋር በትብብር የሚዘጋጀው ኮንፍረንስ በዚህ ማዕቀፍ የሚደረግ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡ በመግለጫው ላይ የጋዛን ወቅታዊ ሁኔታ በማንሳት የእስራኤል ወታደሮች የጀመሩትን መጠነ ሠፊ ጥቃትም አውግዘዋል፡፡ በድጋሚ የተጀመረውን ጥቃት ለንጹሐን፣ ለምርኮኞች፣ ለቤተሰቦቻቸው እና ለቀጣናው ውድቀት ነው ብለዋል።
በእስራኤል የተጣሰው የተኩስ አቁም ስምምነት በፍጥነት እንዲተገበር ጥሪ ያቀረቡት የፈረንሣይ ፕሬዝዳንት፤ በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቀረበውን የጋዛ ነዋሪዎችን የማፈናቀል ዕቅድ ተቃርነው አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ድርጊቱ “ዓለም አቀፍ ሕግን የሚጥስ” እንዲሁም እስራኤልን ጨምሮ አጠቃላይ የቀጣናው ሰላም ላይ “ከፍተኛ ሥጋት የሚደቅን” መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም ጋዛን መልሶ ለመገንባት ሀገራቸው ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጸዋል፡፡

ማክሮን በግብጽ የተገኙት በጋዛ ጉዳይ ከፕሬዝዳንት ዓብዱልፈታህ አል ሲሲ እና ከዮርዳኖስ ንጉሥ ዓብደላህ ሁለተኛ ጋር ለመምከር ነው፡፡ በጋዛ ጉዳይ የሚመክረው የሦስትዮሽ ጉባኤ በዛሬው እለት እንደሚካሔድ ሚድል ኢስት ሞኒተር ዘግቧል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












