Homeዜናና ወቅታዊዜናሳዑዲ ዐረቢያ፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ 14 ሀገራት ላይ ጊዜያዊ የቪዛ ዕግድ ጣለች

ሳዑዲ ዐረቢያ፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ 14 ሀገራት ላይ ጊዜያዊ የቪዛ ዕግድ ጣለች

የ1446 ዓ.ሂ የሐጅ ሥነ ሥርዐት ዝግጅት መጀመሯን ባለፈው ሣምንት ይፋ ያደረገችው ሳዑዲ ዐረቢያ፤ በ14 ሀገሮች ላይ ጊዜያዊ የሌሎች ቪዛ ዐይነቶች እግድ መጣሏን ይፋ አደረገች፡፡ ዕግዱ “የዑምራ፣ የንግድ እና የቤተሰብ ጥየቃ” ቪዛን ያካተተ ነው፡፡

ከሐጅ ጉዞ ጅማሮ አስቀድሞ የተጣለው ዕግድ፤ በቅዱሳኑ መካ እና መዲና ከተሞች “የሚኖረውን መጨናነቅ ለመቀነስ” በሚል የተወሰደ መሆኑን የሀገሪቱ ባለሥልጣናትን ዋቢ በማድረግ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡ እንደ ዘገባዎቹ ከሆነ፤ ዕግዱ እስከ ሰኔ እኩሌታ ድረስ ተግባራዊ የሚደረግ ነው፡፡ በዚህ የጊዜ ሠሌዳ መሠረት ዕግዱ የሐጅ ሥነ ሥርዐት እስከሚጠናቀቅ ይቆያል፡፡

በቪዛ ዕግዱ የተካተቱት ኢትዮጵያን ጨምሮ አልጄሪያ፣ ባንግላዴሽ፣ ግብጽ፣ ሕንድ፣ ኢንዶኔዥያ፣ኢራቅ፣ ዮርዳኖስ፣ ሞሮኮ፣ ናይጄሪያ፣ ፓኪስታን፣ ሱዳን፣ ቱኒዚያ እና የመን ናቸው። በውሳኔው መሠረት ሐጅ እስኪጠናቀቅ ድረስ የሐጅ እና ዑምራ ሚኒስቴር ለተጠቀሱት ሀገሮች ዜጎች ማንኛውንም አዲስ ቪዛ አይሰጥም።

ባለሥልጣናቱ ባለፈው ዓመት የሐጅ ወቅት ከ1 ሺሕ 200 በላይ ምእመናን ላይ ለተከሰተው ሞት መንስኤ ነው ለተባለው “ከፍተኛ የሙቀት መጠን እና መተፋፈግ” ተጠያቂ ያደረጉት “ለሐጅ በሕጋዊ መንገድ ያልተመዘገቡ” ተሳታፊዎችን ነው። እነዚህ ያልተመዘገቡ ምዕመናን እንደ ማረፊያ፣ መጓጓዣ እና የጤና ክብካቤ ያሉ አስፈላጊ አገልግሎቶችን ማግኘት አይችሉም፡፡ ይህም “የደኅንነት ሥጋቶችን የሚጨምር” መሆኑን ባለሥልጣናት ይናገራሉ፡፡

የሳዑዲ ዐረቢያ የሐጅ እና ዑምራ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፤ የተወሰደው ርምጃ “ደኅንነቱ የተጠበቀ የሐጅ ጉዞ ለማቅረብ የሚያስችል የሎጂስቲክስ ምላሽ መስጠትን” ታሳቢ ማድረጉን በመግለጽ፤ “ከዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ጋር ምንም ግንኙነት” እንደሌለው አያይዞ ገልጿል፡፡

የሀገሪቱ ባለሥልጣናት ግለሰቦች ያለፍቃድ ሐጅ ቢፈጽሙ አልያም በሌሎች ቪዛዎች ገብተው ከተፈቀደላቸው ጊዜ በላይ ቢቆዩ፤ ለአምስት ዓመት ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ እንዳይገቡ ይደረጋል ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡ ባለፈው ዓመት በሐጅ ሥነ ሥርዐት ክንውን ላይ በሕጋዊ ምዝገባ የተሳተፉ ምዕመናን ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ መሆናቸውን ይፋዊ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ የሐጅ ተጓዦች ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ የሚያደርጉት ጉዞ የሚጀምረው ከሚያዝያ 14 እስከ 20/2017 ባሉት ቀናት እንደሚሆን የሐጅ እና ዑምራ ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል፡፡ ሚኒስቴሩ ለዓመታዊው ክንውን ዝግጅት የሐጅ እና ዑምራ ሚኒስቴር ከሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጋር በመተባበር በዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ምዕመናንን የሚያጓጉዙ ዓለም አቀፍ በረራዎችን ለማቀላጠፍ እየሠራ መሆኑን ገልጿል፡፡ በዘንድሮው የሐጅ ሥነ ሥርዐት ላይ 10 ሺሕ ኢትዮጵያውያን ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከዚህ ቀደም አስታውቋል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular