ማማዱ ተአል የዘር ግንዱ የሚመዘዘው ከምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ጋምቢያ ነው፡፡ የዘር ግንዱ በሚመዘዝበት ሙስሊሞች በሚበዙበት በዚያ፤ “ማማዱ” ማንዴ እና ዎሎፍ በተሠኙ ጎሳዎች የተለመደ የወንዶች መጠሪያ ነው፡፡ “ማማዱ” – ልክ እንደ ዐረቢኛው “ሙሐመድ”፤ ወደ አማርኛ ሲመለስ “ምሥጉን” የሚል አቻ ፍቺ አለው፡፡ በዜግነት እንግሊዛዊው የ31 ዓመቱ ወጣት፤ እስከባለፈው ሰኞ ድረስ ኑሮውን ያደረገው በአሜሪካን ሀገር ነበር፡፡
እዚያ የወሰደው ትምሕርት ነው፡፡ በኮርኔል ዩኒቨርሲቲ ሦስተኛ ዲግሪውን ‘በአፍሪካና ስተዲስ’ ትምሕርት ክፍል ይከታተላል፡፡ ከተማሪነቱ ጎን ለጎን እንደ ሥሙ የሚያስመሠግነው ተግባር ላይ የተሠማራ ነው። ማማዱ በአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ለፍልስጤማዊያን ድምጽ ከሆኑ ተማሪዎች መካከል ከፊት ረድፍ አይታጣም። ፍልስጤማዊያንን የሚደግፉ ሠልፎችን ያስተባብራል፤ የሚማርበት ዩኒቨርሲቲ ለእስራኤል የጦርነት ማገዶ ማዋጣት የለበትም ሲል አስተዳደሩን ይሞግታል፡፡ ይህን የሚያደርገው ደጋግሞ ነው፡፡ ሆኖም የማማዱ ተአል በዚህ መንገድ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ በዩኒቨርሰቲው ኃላፊዎች፤ ከዚያም አለፍ ሲል በአሜሪካ ባለሥልጣናት አልተወደደለትም፡፡
የኮርኔል ዩኒቨርሲቲ በመስከረም ወር መጀመሪያ ላይ በካምፓሱ ውስጥ የተካሄደ ሞያ ነክ አውደ ርዕይ ላይ ሁከት በመፍጠር ክስ አቅርቦበት የእግድ ውሳኔ አሳለፈ፡፡ በወቅቱ የተላለፈው ውሳኔ ማማዱን የተማሪ ቪዛው ተሠርዞ ወዲያውኑ የአሜሪካ መሬት ለቆ እንዲወጣ የሚያደርገው ነበር። ይግባኝ በመጠየቁና ተቃውሞውም ስለበረታ ውሳኔው ከሁለት ሣምንት በኋላ ተሻሽሎ ከመሠናበት ተረፈ፡፡
ዩኒቨርሲቲው በወቅቱ ስላሳለፈው ውሳኔ ለመገናኛ ብዙኃን የተናገረው ማማዱ፤ “ውሳኔውን ማቃለል አልፈልግም፤ የተጋነነ ደስታ ውስጥ የሚከተኝም አይደለም” ብላል፡፡ “ውሳኔው ያደረገው ነገር ቢኖር ከሁለት ሳምንት በፊት ከሀገር ልባረር የነበረ ቢሆንም አሁንም እንድቆይ መፍቀዱ ነው” ሲል ያክላል፡፡ ተአል ይህን የሚለው በሀገሪቱ ቢቆይም ወደ ዩኒቪርሲቲ ቅጽር ግቢ መግባት ስላልተፈቀደለት ነበር፡፡ በዚህ ብቻ ሳያበቃ ከፒኤችዲ ጥናቱ ጎን ለጎን ሲያስኬደው የቆየውን የመምሕርነት ሥራ እንዳይሠራ በመታገዱም ነው፡፡ ስለሁኔታው ለሚድል ኢስት ዐይ ሲናገር፤ “የቤት ውስጥ እስር እንደማለት ነበር” ሲል ገልጾታል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ይህን ውሳኔ ሲያሳልፍ በርካቶች ከማማዱ ተአል ጎን ቆመዋል፡፡ ‘ስቱደንትስ ፎር ጀስቲስ ኢን ፓለስታይን አት ኮርኔል’ ፕሬዝዳንት ማሊክ አቡሐሺም፤ የማማዱ ተአል እግድ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በሚገኙ የውጭ አገር ተማሪዎች ላይ አስደንጋጭ ተጽዕኖ ማሳደሩን ይናገራል። ይህን በምክንያት ሲደግፈው፤ የእርሱ እግድ ሌሎች ከፍልስጤም ጎን በመቆም ድምጽ በማሰማታቸው ከትምሕርት ልንፈናቀል አልያም ከሀገር ልንባረር እንችላለን የሚል ሥጋት ማሳደሩን በማንሳት ነው።
ማማዱ ተአል በዚህ ሁኔታ ውስጥ ባለበት የሚኖርበት አሜሪካ ምርጫ በማካሔድ፤ አወዛጋቢው ዶናልድ ትራምፕ በኅዳር ወር መገባደጃ ወደ ፕሬዝዳንት መንበር ተመለሱ፡፡ ፕሬዝዳንቱ የተለመዱ አወዛጋቢ ውሳኔዎችን ማሳለፍ የቀጠሉት ወዲያውኑ ነበር፡፡ ከእነዚህ መካከል አንደኛው የነበረው በእስራኤል የዘር ማጥፋት ወንጀል ላይ በሚሰነዘሩ ተቃውሞዎች እና እንቅስቃሴዎች ላይ የሚሳተፉ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ዒላማ የሚያደርገው ትእዛዝ ነው፡፡ ትእዛዙ የመንግሥት ኤጀንሲዎች የፌዴራል የሲቪል መብቶች ቅሬታዎችን በሚመረምሩበት ጊዜ እስራኤልን የሚተቹ ንግግሮችን በሙሉ ከግምት ውስጥ እንዲያስገቡ መመሪያ ይሰጣል፡፡

ይህን የትራምፕን ውሳኔ ማማዱ ተአል በዝምታ ሊያልፈው አልፈቀም፡፡ ከሌላ የዶክትሬት ተማሪ እንዲሁም አንድ ፕሮፌሰር ጋር በመሆን ከውሳኔዎች መካከል ሁለቱን ለማስፈጸም የሚደረገው ሒደት የሚጥሳቸው ድንጋጌዎች ይኖራሉ ሲሉ ትእዛዝ በመቃወም ክሥ መሠረተ፡፡ ማማዱ ተአል እና ባልንጀሮቹ በክሱ ላይ አዲሱን ትእዛዝ በመቃወም ለፍልስጤማዊያን ድምጽ በመሆናቸው “መንግሥት በራሳችንም ጭምር የበቀል ርምጃ ይወሰድብናል” የሚል ሥጋት እንዳላቸው ገልጸው ነበር፡፡
እነ ማማዱ የፈሩት አልቀረም፡፡ የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተአል ወደ ሀገሪቱ ሲገባ የተሰጠውን ኤፍ 1 የተሠኘ ቪዛ ክሱ ለፍርድ ቤት ከመቅረቡ አንድ ቀን አስቀድሞ እንዲሠረዝ አደረገ፡፡ ከውሳኔው በኋላ ቪዛውን ለማስመለስ ጠበቆቹ ቢሟገቱም አልተሳካላቸውም፡፡
በዚህ መነሻ ማማዱ ተአል ባለፈው ሰኞ አሜሪካን ለቆ ለመውጣት መወሰኑን በኤክስ ገጹ ላይ ይፋ አደረገ፡፡ “በትራምፕ አስተዳደር ላይ ክስ ያቀረብኩት ለእኔ እና መሰሎቼ የፍትሕ ጥማት ማስታገሻ ነበር” ያለው ማማዱ፤ “ፕሬዝዳንቱ ግን በችሎት እንኳን እንድገኝ ስላልፈለጉ የደኅንነት ወኪሎችን በመላክ ቪዛዬ እንዲሰረዝ አድርገዋል” ሲል አስፍሯል፡፡
የኮርኔል ተማሪው የፍልስጤም ደጋፊ አሜሪካን ለቆ የወጣው በፍርድ ሒደቱ ላይ አመኔታ ከማጣቱ በተጨማሪ “በመንገድ ላይ ስጓዝ አፍነው እንደማይወስዱኝ ርግጠኛ መሆን አልቻልኩም” በሚል ነው። የትራምፕ አስተዳደር ሲፈጽም የነበረው ነገር ሁሉ ከሕግ ውጭ እንደነበርም ተናግሯል፡፡ በሀገሪቱ ቢያንስ ክርክሩ እስኪቋጭ የመቆየት እድል ቢኖረውም “ፍርድ ቤት ለእኔ ቢወስን እንኳን ከዚያ በኋላ በጎዳናዎች ላይ በነጻነት ለመራመድ ማስተማመኛ የለኝም” ሲል የሥጋቱን መጠን ያብራራል፡፡

የተአል ጉዳይ በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ አፍሪካ ሪፖርት ቡድኖቹ የዶክትሬት ተማሪው አሜሪካ ለቆ መውጣት በተለይም የፍልስጤም ደጋፊዎችን ትግል የሚያደናቅፍ መሆኑን በመጥቀስ ሥጋት እያጋሩ እንደሚገኙ አስነብቧል፡፡ የመብት ተሟጋቾቹ ይህን ቢሉም የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ከቀናት በፊት ከ300 በላይ የሚሆኑ ዓለም አቀፍ ተማሪዎች በፖለቲካ አመለካከታቸው ላይ ተመሥርተው እንዲባረሩ ወይም ቪዛቸው እንዲሠረዝ መደረጉን በመግለጽ መርዶ ጨምረዋል።
በዚህ አግባብ ባለፉት ሳምንታት ይፋ በተደረጉ መረጃዎች ከማማዱ ተአል በተጨማሪ፤ ፍልስጤማዊው የኮሎምቢያ ዩኒቨርሰቲ ተማሪ ማሕሙድ ኸሊል ለእስር ተዳርጓል፡፡ ኸሊል ቋሚ የአሜሪካ መኖሪያ ወረቀት እንዳለው የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ ያመለክታል፡፡ የቱፍትስ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዋ ቱርካዊቷ ሩመይሳ ኦዝቱርክ በተመሳሳይ ሐማስን ትደግፋለች የሚል ውንጀላ ቀርቦባት በደኅንነቶች መኖሪያ ቤቷ ተበርብሯል። የደቡብ ኮሪያ ዜግነት ያላት የ21 ዓመቷ ዩንሲኦና ሌሎችም የፍልስጤም ደጋፊ የአሜሪካ ዩኒቨርሰቲ ተማሪዎች ከሀገሪቱ የመባረር ዕጣ ከፊት ተጋርጦባቸዋል።
በተማሪዎቹ ላይ አደጋ ቢጋረጥም ለአፍሪካ ሪፖርት “ማንንም ሳይሰናበት” ሀገሪቱን ለቆ መውጣቱን የተናገረው ማማዱ ተአል፤ አሜሪካን በግዳጅ ቢሰናበትም ባለበት በመሆን ለፍልስጤማዊያን ድምጽ ማሰማቱን እንደሚቀጥል ገልጿል። ይህን ሲናገር፤ “የፍልስጤም ተሟጋችነት ጅማሮም ሆነ የሚቆምው በአሜሪካ መሬት ላይ አይደለም፤ ዓለም አቀፋዊ ነው፤ እኔም በዓለም አቀፍ ደረጃ ትግሌን እቀጥላለሁ” በማለት ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












