በሕንድ የጸደቀው የ“ወቅፍ” አስተዳደር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ከሙስሊም የመብት ተሟጋቾች እና ከሀገሪቱ መንግሥት ተቀናቃኝ የፖለቲካ ቡድኖች ተቃውሞ አስተናገደ፡፡ በሀገሪቱ ከግለሰቦች እና ከተለያዩ አካላት የሚበረከተውን “ወቅፍ” የሚተዳደርበትን ሕግ የሚሽረው አዲሱ ማሻሻያ፤ በቦርድ ውስጥ ሙስሊም ያልሆኑ ግለሰቦች እንዲካተቱ የሚፈቅድ ነው፡፡
ረቂቅ አዋጁ በዛሬው እለት የፀደቀው፤ በሀገሪቱ ከፍተኛው ምክር ቤት ‘ሪጃ ሳባን’ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የሙስሊም ማኅበረሰብ እና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ረቂቁ “የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ የጣሰ” እንዲሁም በሀገሪቱ ውስጥ በቁጥር አናሳ ነው የሚባለውን “የሙስሊሙን ማኅበረሰብ መብት የሚጋፋ ነው” ሲሉ ነቀፌታ ሰንዝረውበታል፡፡ ረቂቅ ሕጉ ተግባራዊ ሲደረግ መስጂዶችን ጨምሮ በሀገሪቱ በወቅፍ መልክ የተበረከቱ ኢስላማዊ ቅርሶችንና የቀብር ሥፍራዎችን ጭምር ከሙስሊሞች ሊነጥቅ ይችላል በሚል ሥጋት ፈጥሯል፡፡
የመንግሥት ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ሕጉ ተግባራዊ እንዳይደረግ በፍርድ ቤት ክስ እንደሚመሠርቱ ገልጸዋል፡፡ የሕንድ ኮንግረስ ከፍተኛ አመራሩ ጀይራም ራሜሽ፤ የወቅፍ ማሻሻያው ሲደረግ የሕገ መንግሥት ጥሰት መፈጸሙን በመጠቆም፤ በቅርቡ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ክስ እንደሚመሠርቱ ማረጋገጫ መስጠታቸውን የሚድል ኢስት ሞኒተር ዘገባ ያመለክታል፡፡ የኮንግረሱ ፕሬዝዳንት ማሊካርጁን ካርጌም እንዲሁ “አናሳዎችን ለማሰቃየት የተዘጋጀ ነው” ያሉትን የሕግ ረቂቅ አውግዘውታል፡፡
የረቂቅ ሕግ ማሻሻያው በሙስሊም የሲቪል ማኅበረሰብ ቡድኖችም ከፍተኛ ተቃውሞ ቀርቦበታል፡፡ “ጀማዕቲ ኢስላሚ ሒንድ” የተሰኘው የሙስሊሞች መብት ተሟጋች ድርጅት፤ የሕጉ መጽደቅ “የሃይማኖት ነፃነት እና ሕገ መንግሥታዊ መብቶች ላይ የተሰነዘረ ቀጥተኛ ጥቃት ነው” ብሎታል። የድርጅቱ ፕሬዝዳንት ሲዬድ ሳዳቱላህ ሑሰይኒ፤ “መንግሥት በሕንድ የአናሳ ማኅበረሰቦችን መብት እየደፈጠጠ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎች በወቅፍ ቦርዶችና ፍርድ ቤቶች እንዲሾሙ የሚፈቅደው ረቂቅ አዋጁ፤ እ.አ.አ በ1995 ፀድቆ በሥራ ላይ የነበረውን የወቅፍ ፍርድ ቤቶች ውሳኔ የመጨረሻ ተደርገው የሚታዩበትን አሠራር በመሻር በንብረት ክርክር ሒደት መደበኛ ፍርድ ቤቶች በዳኝነት ጣልቃ እንዲገቡ ይፈቅዳል። ረቂቅ ሕጉ በወቅፍ አስተዳደር ላይ ከሃይማኖት ተቋማት ይልቅ መንግሥት ከፍተኛውን ሚና እንዲይዝ የሚያደርግ መሆኑንም አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
ረቂቅ ሕጉ ተቃውሞ ቢቀርብበትም በጠቅላይ ሚኒስትር ኔራንድራ ሞዲ የሚመራው የሀገሪቱ መንግሥት፤ ሕጉ የተሻሻለው የወቅፍ አስተዳደር በተሻለ ግልጽነት እንዲመራ ነው የሚል መከራከሪያ አቅርቧል፡፡ የመንግሥቱ ባለሥልጣናት ይህንኑ በመገናኛ ብዙኃን ፊት ቀርበው ቢያስረዱም በተቃራኒው ሕጉ መስጂዶችን ጨምሮ ታሪካዊ ኢስላማዊ ቅርጾችን መንግሥት ሕጉን በመጠቀም ለመውረስ እንዲያመቸው ያደረገው ነው በሚል በሥጋት የሚመለከቱት በርካቶች መሆናቸውን ዘገባዎች አመላክተዋል፡፡
ከሕንድ አጠቃላይ ሕዝብ የሙስሊሞች ቁጥር 14.2 በመቶ ብቻ ሰነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












