የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፤ የ1446 ዓ.ሂ የሐጅ ምዝገባ የጊዜ ሠሌዳን ለሁለተኛ ጊዜ ማራዘሙን የገለጸው በዛሬው ዕለት ባወጣው መረጃ ነው፡፡ ምክር ቤቱ ምዝገባው እንደሚቀጥል ቢገልጽም የጊዜ ገደብ ስለማስቀመጡ የጠቀሰው ነገር የለም፡፡
ምክር ቤቱ የሐጅ ምዝገባ የጊዜ ሠሌዳ በድጋሚ ያራዘመው “ለማጣሪያ እና ለኮታ ማሟያ” መሆኑን ቢገልጽም፤ “የተሟላ መረጃ ያላቸውና በተለያዩ ምክንያቶች ምዝገባ ያልፈጸሙ [ምዕመናን] አስፈላጊ መረጃዎችን ይዘው በመቅረብ” መመዝገብ እንደሚችሉ አስታውቋል፡፡
ከዛሬ ሐሙስ መጋቢት 25/2017 ጀምሮ በሁሉም የምዝገባ ጣቢያዎች በድጋሚ እንዲቀጥል የተወሰነው የሐጅ ምዝገባ፤ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ መጋቢት 20 ተጠናቆ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የጠቅላይ ምክር ቤቱ የሐጅ እና ዑምራ ዘርፍ፤ በሒደቱ “የተወሰኑ ተመዝጋቢዎች ማሟላት የሚገባቸውን መረጃዎች አሟልተው አመቅረባቸውን ባደረግነው ማጣሪያ ማረጋገጥ ችለናል” ብሏል፡፡
ለተመዝጋቢዎች “ሌላ የምዝገባ ዕድል መስጠት አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት” ይቀጥላል የተባለው የሐጅ ምዝገባ፤ ዛሬ ሐሙስ መጋቢት 25/2017 እንደሚቀጥል ቢገለጽም የጊዜ ገደብ ስለመቀመጡ የተጠቀሰ ነገር የለም፡፡
በምዝገባው “የተሟላ መረጃ ያላቸውና በተለያዩ ምክንያቶች ምዝገባ መፈጸም ካልቻሉ ምዕመናን በተጨማሪ፤ “ከዚህ በፊት ተመዝግበው መረጃ ያላሟሉና ከሲስተም እንዲወጡ የተደረጉ ሑጃጅ የተጓደሉ መረጃዎችን በሟማላት” መመዝገብ ይችላሉ ተብሏል፡፡ “በአካል መገኘት ባለመቻላቸው ስልክ በመደወል የተመዘገቡ ምዕመናንም በጊዜ ማራዘሚያው ተጠቅመው ምዝገባ ማካሄድ እንደሚችሉ” ተገልጿል፡፡
ጠቅላይ ምክር ቤቱ የዘንድሮውን የሐጅ ምዝገባ የጀመረው ጥር 15/2017 ነበር፡፡ ቀድሞ በተቀመጠው የጊዜ ሠሌዳ መሠረት ምዝገባው ከረመዳን ወር አስቀድሞ እንደሚጠናቀቅ የጊዜ ገደብ ቢቀመጥም በረመዳን ወር እንዲቀጥል ተደርጓል፡፡
በዘንድሮው የሐጅ ሥነ ሥርዐት ክንውን ላይ ከኢትዮጵያ ይሳተፋሉ ብሎ በእቅድ ያስቀመጠው 10 ሺሕ ሑጃጅ መሆኑ ቀድሞ ተገልጿል፡፡ ነገር ግን እስካሁን የተመዘገቡት ምዕመናን ቁጥር የተቀመጠውን ኮታ የሚሞላ ስለመሆኑ ይፋ ያደረገው መረጃ የለም፡፡ “ሚንበር ቲቪ” በመጀመሪያ ዙር ምዝገባ የተመዘገቡ ምዕመናን ቁጥር 4 ሺሕ 12 እንደነበር መዘገቡ የሚታወስ ነው፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የካቲት 4/2017 በሰጠው መግለጫ፤ የሐጅ ጉዞ ክፍያ 625 ሺሕ ብር መሆኑን ገልጿል፡፡ ክፍያው ባለፈው ዓመት ከነበረው 329 ሺሕ ጋር ሲነፃፀር ወደ 90 በመቶ ገደማ ጭማሪ የታየበት ነበር፡፡ ምክር ቤቱ በወቅቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ለጭማሪው መከሰት የጠቀሰው የብር የመግዛት አቅም መዳከሙን ነው፡፡
ባለፈው ዓመት ከኢትዮጵያ ለሐጅ ሥነ ሥርዐት ክንውን ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ የተጓዙ ምዕመናን ቁጥር 12 ሺሕ ነበር፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












