መቀመጫውን አሜሪካ ኒውዮርክ ያደረገው ዓለም አቀፉ የመብቶች ተሟጋች ሂዩማን ራይትስ ዎች፤ ወደ ሀገሯ ለጉብኝት የገቡትን የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁን በቁጥጥር ስር እንድታውል ጠይቋል፡፡ ኔታንያሁ ለአራት ቀናት ጉብኝት ሀንጋሪ መዲና ቡዳፔስት ገብተዋል፡፡
የመብት ተሟጋቹ ይህን የጠየቀው ኔታንያሁ ዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት በኅዳር ወር የእስር ማዘዣ ካወጣ በኋላ ወደ ሀንጋሪ የመጀመሪያውን ጉዞ ሊያደርጉ መሆኑ ከተሰማ በኋላ ነው፡፡ ሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በቁጥጥር ስር እንድታውል የተጠየቀችው፤ የወንጀል ፍርድ ቤቱ አባል በመሆኗ ነው፡፡
ሂዩማን ራይትስ ዎች ጉብኝቱን ተቃውሞ ባወጣው መግለጫ፤ “ሀንጋሪ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ወደ ሀገሯ እንዳይገቡ መከልከል አለባት፤ እንዲገቡ ከፈቀደች ደግሞ በቁጥጥር ስር ማዋል ይኖርባታል” ብሏል፡፡ አክሎም ሀንጋሪ የዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት አባል ሀገር እንደመሆኗ መጠን፤ “ወደ ግዛቷ የሚገቡ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋልና አሳልፎ ለመስጠት የመተባበር ግዴታ አለባት”። ፍርድ ቤቱ የፖሊስ ኃይል ስለሌለው “ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር የማዋል ኃላፊነት በአባል ሀገሮች ላይ እንደሚወድቅ”ም ገልጿል፡፡
ኔታንያሁ ወደ ሀንጋሪ ያመሩት በሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ሚሃሊ ኦርባን ግብዣ መሆኑን የሲኤንኤን ዘገባ ያመለክታል፡፡ ለአራት ቀናት የሚቆየውን ጉብኝት ለማድረግ ረቡዕ መዲናዋ ቡዳፔስት መድረሳቸው ተነግሯል፡፡ በሂዩማን ራይትስ ዎች የዓለም አቀፍ ፍትሕ ዳይሬክተር ሊዝ ኤቨርሰን፤ ሀንጋሪ ለኔታንያሁ ያቀረበችው ግብዣ፤ “ለከባባድ ወንጀል ሰለባዎች እንደ ስድብ የሚቆጠር ነው” ብለውታል፡፡ ድርጊቱ ኦርባን እና መንግሥታቸው ለሕግ የበላይነት እና ለሰብዓዊ መብቶች “ከፍተኛ ንቀት ያሳዩበት” እንደሆነ በመግለጽም ተችተውታል፡፡
በመብት ተሟጋቹ ተቃውሞ የቀረበባት የሀንጋሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ሚሃሊ ኦርባን፤ በአክራሪ ቀኝ ዘመም ብሔርተኛነት የሚታወቁ ፖለቲከኛ ናቸው፡፡ ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት በኅዳር ወር በኔታንያሁ ላይ የእስር መዘዣ ባወጣበት ወቅት ውሳኔውን በመቃወም ሰውዬው ወደ ሀገራቸው እንዲመጡ ግብዣ እንደሚያቀርቡላቸውና ከለላ እንደሚሰጡም ጭምር የሚገልጽ አወዛጋቢ ንግግር አድርገው ነበር፡፡ ይኸው ግብዣ ከመብት ድርጅቶች ነቀፌታ ተሰንዝሮበታል፡፡
ሀንጋሪ ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ያሳለፈውን የእስር ማዘዣ ባለመቀበል የእስራኤሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ሀገሯ የመጋበዝ ዜና ከተሰማ በኋላ፤ ሀገሪቱ ከፍርድ ቤቱ አባልነት ልትወጣ እንደምትችል እየተነገረ ይገኛል፡፡
ሚድል ኢስት ዐይ እንደዘገበው፤ ሀንጋሪ ፍርድ ቤቱ ሲቋቋም የፈረመችውን የሮም ስምምነት በመቅደድ ከአባልነት የምትለቅ የመጀመሪያው የአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገር ትሆናለች፡፡ በሮማ ስምምነት አንቀፅ 127 መሠረት ሀንጋሪ ከስምምነቱ ለመውጣት ለተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ በጽሑፍ ጥያቄ ማቅረብ ይኖርባታል፡፡ ድርጅቱ ጥያቄውን ከተቀበለ ከአንድ ዓመት በኋላ ከአባልነት የመልቀቅ ውሳኔ ተግባራዊ የሚደረግ ይሆናል፡፡ ሀገሪቱ ይህን ውሳኔ የምታሳልፈው የእስራኤሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ወንጀል ለመሸፋፈን ነው በሚል ከሂዩማን ራይትስ ዎች በተጨማሪ አምነስቲ ኢንተርናሽናልም ተቃውሞ አሰምቷል፡፡
ዓለም አቀፉ ወንጀል ፍርድ ቤት ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር በተጨማሪ በቀድሞ መከላከያ ሚኒስትር ዮቭ ጋላንት ማውጣቱ የሚታወስ ነው፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












