1/ ከፍተኛ የሙስሊም ዜጎች ቁጥር ባለባት ኢንዶኔዥያ የዒድ አልፊጥር በዓል ደብዛዛ ሆኖ ማለፉ ተዘግቧል። ለበዓሉ መቀዛቀዝ በምክንያት የተጠቀሰው የሸቀጣ ሸቀጥ፣ አልባሣት እና ሌሎች ተፈላጊ ቁሳቁስ ዋጋ በከፍተኛ መጠን ማሻቀቡ መሆኑን ሳውዝ ቻይና ሞርኒንግ ፖስት በድረ ገጹ አስነብቧል። ዘገባው እንዳመላከተው፤ በርካታ ኢንዶኔዥያዊያን በበዓል ወቅት ቀዬ ተመልሰው የማክበር ልማድ አላቸው። በዚህም ባለፈው ዓመት ወደ ቀዬ የተመለሱ ተጓዦች ቁጥር 194 ሚሊዮን የነበረ ቢሆንም ዘንድሮ በ25 በመቶ መቀነሱን የሀገሪቱ ትራንስፖርት ሚኒስቴር አስታውቋል። የኢንዶኔዥያ ቻምበር ኦፍ ኮሜርስ ባለፈው ዓመት በዒድ ሰሞን የተመዘገበው የ157 ነጥብ ትሪሊዮን ሩፒያህ (8 ነጥብ 33 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገደማ) የገንዘብ ዝውውር፤ ወደ 137 ነጥብ 97 ትሪሊዮን ሩፒያህ አሽቆልቁሏል ብሏል።
2/ በጦርነት ውስጥ የምትገኘው ሱዳን ዜጎች የዒድ አልፊጥርን በዓል ትናንት እሑድ አክብረዋል። በበርካታ የሀገሪቱ አካባቢዎች የቀጠለው ጦርነት ጥላውን ቢያጠላም ባለፉት ቀናት መደበኛው ጦር የተቆጣጠረው መዲናው ካርቱምና በዑምዱርማን አንዳንድ ሥፍራዎች መደብሮች የሕፃናት አልባሣትን ጨምሮ በበዓል ተፈላጊ ቁሳቁስ ሽያጭ ላይ እንደነበሩ የኒው ዐረብ ዘገባ ያመለክታል። ለዜና ምንጩ አስተያየት የሰጠ የዑምዱርማን ነዋሪ የዘንድሮው ሁኔታ ከአምናው ጋር ሲነጻጸር የተለየ መሆኑን ተናግሯል። ከተማዋም ለማንሰራራት ትግል ውስጥ ትገኛለች ሲል አክሏል።
3/ የሳዑዲ ዐረቢያ የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ዘርፍ በዒድ አልፊጥር በዓል ከፍተኛ ዕድገት እንዳስመዘገበ የሀገሪቱ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል። ዐረብ ኒውስ እንደዘገበው፤ በቅርብ ዓመታት በበዓሉ ሰሞን የሚመዘገበው የሀገር ውስጥ በረራ በከፍተኛ መጠን ጭማሪ አሳይቷል። እንደ መረጃው ባለፈው እ.አ.አ በ2024 የሀገር ውስጥ በረራ በቀዳሚው ዓመት ከነበረው 45 በመቶ ዕድገት ተመዝግቦበታል።
4/ ሶሪያዊያን ከበሻር አል አሰድ አገዛዝ መውደቅ በኋላ የመጀመሪያውን የዒድ አልፊጥር በዓል በዛሬው እለት ማክበር ችለዋል። በበዓሉ ላይ የሀገሪቱ አዲሱ ፕሬዝዳንት አሕመድ አሸረዕ፣ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸውን እንዲሁም የፈትዋ ካውንስል መሪ በማስከተል በመዲናዋ ደማስቆ በተከናወነ የዒድ ሰላት ላይ መገኘታቸውን ሚድል ኢስት ዐይ ዘግቧል።
5/ የረመዳን ወር ተጠናቆ ዒድ አልፊጥር ሲታወጅ ሳዑዲ ዐረቢያ በዘንድሮው ሐጅ ሥነ ሥርዐት ላይ መሳተፍ የሚፈልጉ ነዋሪነታቸው በግዛቷ የሆኑ ምዕመናንን መመዝገብ መጀመሯን ይፋ አድርጋለች። የሀገሪቱ ሐጅ እና ዑምራ ሚኒስቴር ባወጣው መረጃ፤ ከዚህ ቀደም በክንውኑ ላይ ተሳትፈው ለማያውቁ ምዕመናን ቅድሚያ በመስጠት ምዝገባ የሚደረገው ‘ኑሱክ’ በተሰኘው መተግበሪያ እና ሌሎች የኤክትሮኒክስ ዘዴዎችን በመጠቀም ነው። ሚኒስቴሩ ለምዝገባው የማጅራት ገትር ክትባት መውሰድን እንደ መሥፈርት ማስቀመጡን የዘገበው ሳዑዲ ጋዜት ነው። (ሚንበር ቲቪ)












