Homeዜናና ወቅታዊሰሞነኛ ጉዳዮችለሐጅ መውጫ በር የተቆለፈባቸው

ለሐጅ መውጫ በር የተቆለፈባቸው

ጥንዶቹ ሙሐመድ ጀርጉን እና ፋጢማ ጀርጉን ቀድመው እንደወጠኑት ቢሆን ኖሮ የሰሞኑ ውሎ እና አዳራቸው የሚሆነው በቅድስቲቱ መካ ከተማ ነበር፡፡ ነገር ግን አልተሳካም፡፡ እቅዳቸው ሳይሰምር በመቅረቱ፣ በመካ ከተማ ሳይሆን በግፈኛ በፈራረሰ መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ተቀምጠው የደረሰባቸውን ይናገራሉ፡፡

የ67 እና 65 ዕድሜ ያላቸው ባል እና ሚስቱ፣ በሰላሙ ጊዜ በፍልስጤም ባለሥልጣናት በኩል የዘንድሮውን ሐጅ ሥነ ሥርዐት ለማከናወን ተመዝግበው ነበር፡፡ መመዝገብ ብቻ አይደለም፤ ሥማቸው ከተመረጡት መካከል የመካተት ዕድል አግኝቶም ነበር፡፡ ጥንዶቹ ሥማቸውን ከሐጅ ተጓዦች ዝርዝር ውስጥ መካተቱን ሲያውቁ፤ ‘የሕይወት ዘመን ምኞታችን ሊሳካ ነው’ በሚል ደስታቸው ወደር እንዳልነበረው ያስታውሳሉ፡፡

ሆኖም እስራኤል በጋዛ ላይ የአፀፋ ያለችውን ጦርነት ስታውጅ የነበረው ሁሉ እንዳልነበረ ሆነ፡፡ ከዚህ በኋላ የንጹሐን ግድያ የዕለት ዜና እንደሆነ ቀጠለ፤ መኖሪያ ቤቶች በከባድ ጦር መሣሪያ ወደሙ፤ የሙሐመድ እና ፋጢማ የሐጅ ውጥንም በጋዛ ከወደመው መኖሪያ ቤታቸው ጋር አብሮ ፈራረሰ፡፡ አሁን የእነ ሙሐመድን መኖሪያ ቤት ወደ ቀድሞ ይዞታው ለመመለስ ቢያንስ 20 ሺሕ ዶላር ይጠይቃል፡፡

ፋጢማ ለአልጀዚራ ጋዜጠኛ ስትናገር ለሐጅ ጉዞ ጌጣ ጌጦቿን ጭምር በመሸጥ ነበር ዝግጅት ያደረገችው፡፡ ሆኖም የራፋ መውጫ ሲዘጋ የእርሷ እና የባሏ ሕልም ይበልጥ ጨለመ፡፡ ባልየው ሙሐመድ ስለ ሁኔታው ሲያስረዳ፤ “ሕመማችን መልከ ብዙ ነው፤ ጦርነት፣ የንብረት ውድመት፣ ከበባ እና ሐጅ ማድረግ አለመቻል ጭምር ነው” ሲል የደረሳቸውንም ይዘረዝራል፡፡ ሙሐመድ ብስጭቱን በገለጸበት ንግግሩ ይበልጥ ሕመም የሆነበት ጉዳይ ሐጅ አለማድረጉ መሆኑን ያብራራል፡፡ ሙሐመድ “እኛ አሁን የምንገኘው በዕድሜያችን አመሻሽ ላይ ነው፤ የራፋህን ድንበር ሲዘጉት አብሮ የተቆለፈበት የሕይወት ዘመን ሕልማችን ጭምር ነው” ብሏል፡፡ ባልየው ሙሐመድ የጋዛ መግቢያ እና መውጫው በመዘጋቱ ኑሯቸውን ልክ እንደ እስር ቤት መሆኑን ተናግሯል፡፡

ሙሐመድ እስር ቤት ሆናለች ባላት ጋዛ ላይ እስራኤል ከመስከረም 26 አንስቶ በሰነዘረችው ጥቃት ቢያንስ 37 ሺሕ ንጹሐን ተገድለዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ ሕፃናት እና እናቶች በርከታ ያለውን ቁጥር ይይዛሉ፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular