Homeዜናና ወቅታዊሰሞነኛ ጉዳዮችበ‘ሕግ ሥም’ የሚበደል ሕግ

በ‘ሕግ ሥም’ የሚበደል ሕግ

ሞንፋልኮኔ ትንሽዬ የጣሊያን ከተማ ነች፡፡ ስደተኛ እና የጉልበት ሠራተኛ ይበዛታል፡፡ መውለድ ብርቅ እየሆነባት ነው በምትባለዋ ጣሊያን፣ በሞንፋልኮኔ ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች ብዛት ከሠላሳ ሺሕ መሻገሩ በግርምት ይወራል፡፡ ከተማዋ ከሀገሬው ሰው ይልቅ የሚበዛው ከሀገር ውጭ የገባ ስደተኛ ነው፡፡ የባንግላዴሽ ዜጎች ቁጥር ደግሞ በርከት ይላሉ፡፡

ይህች ትንሽ ከተማ ከሰባት ወር ወዲህ ሥሟ በአደባባይ እየተነሳ ይገኛል፡፡ በመልካም አይደለም፤ በጥፋት ነው፡፡ ሙስሊሞችን እየበደለች ነው፡፡ በደሉ የሚፈጸመው ደግሞ በከንቲባዋ ነው፡፡ ከንቲባዋ አና ማሪያ እልም ያለች ጽንፈኛ ቀኝ ዘመም ፖለቲከኛ ናት ይሏታል፡፡ ስደተኛም እንዲበዛ አትፈልግም በሚል ሥሞታ የሚቀርብባት ናት፡፡

ከንቲባዋ ከኅዳር ወር አንስቶ በከተማዋ የሚገኙ ሙስሊሞች ለሰላት በሚጠቀሙበት ማዕከል ከዚህ በኋላ መስገድ አይቻልም ብላለች፡፡ በዚህ ምክንያት የከተማዋ ሙስሊሞች በተለይ ሳምንታዊውን የጁመዓ ሰላት በግለሰብ የተሸከርካሪ ማቆሚያ ግቢ ውስጥ ለመስገድ ተገደዋል፡፡ ከንቲባዋ ማዕከላቱ እንዲዘጉ ውሳኔ ስታሳልፍ፣ ነዋሪቹን ያላሳመነ ደንብ አጣቅሳ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የሞንፋልኮኔ ከተማ ነዋሪዎች የዛሬውን ጁመዓ ጭምር የሚሰግዱት በዚህ ሥፍራ ነው፡፡ ለጁመዓ ሰላት ሥፍራውን ያመቻቸው የመኪና ማቆሚያው ባለቤት ረጃዑል ሐቅ፣ ወደ ጣሊያን ያቀናው እ.አ.አ በ2006 ነበር፡፡ አሁን በዜግነት ጣሊያናዊ ነው፡፡

ረጃዑል ሐቅ ከከንቲባዋ ውሳኔ በኋላ ለጠየቁት ጋዜጠኞች ግብር ‘ከምከፍልበት ሀገር ወዴት እንድንሄድ ነው የሚፈልጉት?’ ሲል ተደምጧል፡፡ ሌላኛው የሞንፋልኮኔ ሙስሊም ነዋሪ አንጂነሩ ኮናቴም የረጃዑል ሐቅን ሐሳብ ሲያጠናክር፣ ከንቲባዋ እንዲዘጋ ውሳኔ ያሳለፈችባቸው ሁለት የሙስሊም ማዕከላት ጥቅመ ብዙ መሆናቸውን ያብራራል፡፡ እንደ ኮናቴ ከሆነ ማዕከሉ ከመስገጃነት ባለፈ ሙስሊም ነዋሪዎች ሲከፉም ሆነ ሲደሰቱ የሚሰበሰቡበት ነው፡፡ ስጋት እና ተስፋቸውንም የሚጋሩት በእነዚህ ማዕከላት ነው፡፡ የእነ ረጃዑል ሐቅ እና ኮናቴ ልጆች ከትምህርት ቤት ሲመለሱ ተጨማሪ የዲን ትምህርት የሚቀስሙትም እዚያው ነው፡፡

አሁን እነ ረጃዑል ሐቅ ከከተማዋ ሙስሊም ነዋሪዎች ጋር ባንድነት መብታቸውን በፍርድ አደባባይ ለማስከበር ስለቆረጡ፣ ጉዳያቸውን ፍርድ ቤት ወስደውት እየተሟገቱ ነው፡፡ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ምናልባትም ዛሬ ጁመዓ ይፋ ሊደረግ ይችላል፡፡ ውሳኔው የትኛውም ዐይነት ቢሆን የከተማዋ ሙስሊም ነዋሪዎች ትግል የሚቆም አይመስልም፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular