ሞሳድ በመባል የሚጠራው የእስራኤል የስለላ ድርጅት ዳይሬክተር ዴቪድ ባርኔያ፣ በዚህ ሣምንት ዋሽንግተን ደርሰው ከአሜሪካ ባለሥልጣናት ጋር በተነጋገሩበት ወቅት በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያንን ከጋዛ እንዲወስዱ አሜሪካ የተወሰኑ ሀገሮችን እንድታሳምንላቸው ፍላጎት እንዳላቸው ጥያቄ ማቅረባቸውን አክሲዮስ የተሠኘው በአሜሪካ ፖለቲካ ላይ ሠፊ ሽፋን በመስጠት የሚታወቅ ድረ ገጽ ሁለት ምንጮችን ጠቅሶ አስነብቧል።
የስለላ ኀላፊው ከዋይት ሐውስ የመካከለኛው ምሥራቅ ልዑኩ ስቲቭ ዊትኮፍ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት፤ እስራኤል በተለይ ከሦስት ሀገሮች ጋር ንግግር እያካሄደች ትገኛለች። እነዚህ ሀገሮች ኢትዮጵያ፣ ኢንዶኔዥያ እና ሊቢያ መሆናቸውን ገልፀዋል። ባርኔያ ለዊትኮፍ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሦስቱ ሀገሮች በርካታ ቁጥር ያላቸውን ፍልስጤማውያን ከጋዛ ለመቀበል “ክፍት” መሆናቸውን ገልጸዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ ለእነዚህ ሀገሮች “ማበረታቻ” በመስጠትና በማሳመን ረገድ እገዛ እንድታደርግላቸው ሐሳብ አቅርበዋል። ሐሳቡ የቀረበላቸው ዊትኮፍ “ቁርጠኛ” ምላሽ ባለመስጠታቸው አሜሪካ በጉዳዩ ላይ ንቁ ተሣትፎ ታደርጋለች የሚለው ግልጽ አለመደረጉን ሌላ ምንጭ መናገራቸውን ድረ ገጹ ዘግቧል።
ከጋዛ ማፈናቀል ጋር በተገናኘ ከወራት በፊት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ የከተማዋ ነዋሪዎችን በማፅዳት ቅንጡ ሪዞርት ስለመገንባት የሰነዘሩት አስተያየት፤ ተቃውሞ ባሰሙ ዐረብ ሀገሮች የራሣቸውን ዕቅድ እንዲያቀርቡ ማስገደዱን ያስታወሰው ዘገባው፣ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በዋይት ሐውስ ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ መነሳቱንም ጠቁሟል። በዚህ ወቅት ኔታንያሁ እስራኤል ከጋዛ የሚፈናቀሉ ፍልስጤማውያንን ለመቀበል የሚስማሙ ሀገሮችን ለማግኘት ከአሜሪካ ጋር “በጣም በቅርበት” እየሠራች መሆኑን በመግለጽ፣ “በርካታ ሀገሮችን ለማግኘት እየተቃረብን ነው” ማለታቸው ተጠቅሷል።
ከባለሥልጣናቱ የራት ግብዣ በኋላ አንድ ከፍተኛ የእስራኤል ባለሥልጣን ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፣ ትራምፕ ፍልስጤማውያን ከጋዛ እንዲፈናቀሉ የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ምልክት አሳይተዋል። ይሁን እንጂ ከዋይት ሐውስ በወቅቱ ምንም አስተያየት አልተሰጠበትም።
አክሲዮስ በእስራኤል ሐሳብ ላይ አስተያየት እንዲሰጡበት ለዋይት ሐውስ፣ ለእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እንዲሁም ለኢትዮጵያ፣ ኢንዶኔዥያ እና የሊቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥያቄ ባቀርብም ምላሽ አላገኘሁም ብሏል። (ሚንበር ቲቪ)












