የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተደዳር፤ ግብጽ የጋዛ ነዋሪዎችን ለማፈናቀል እስራኤል ያቀረበችውን ዕቅድ ደግፋ ከኢትዮጵያ ጋር “በሕዳሴ ግድብ የገባችበት አለመግባባት እንዲፈታላት” በአሜሪካ የቀረበላትን ሐሳብ ውድቅ ማድረጓን ከፍተኛ የግብፅ ዲፕሎማሲያዊ ምንጮች ነግረውኛል ብሎ የዘገበው አል አረቢ አልጀዲድ ነው፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ፤ ግብጽ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያንን በራፋህ ድንበር አቅራቢያ በሚገኝ የማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ለማቆየት እስራኤል ያቀረበችውን ዕቅድ መደገፍ ይኖርባታል፡፡ አንድ የግብፅ ዲፕሎማት ለዜና ምንጩ እንደገለጹት፤ የትራምፕ አስተዳደር በምላሹ በኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ ያለውን አለመግባባት ጣልቃ በመግባት እንፈታዋለን የሚል ቃል ገብቷል፡፡
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ሙሉ የፍልስጤምን ሕዝብ ለማስፈር በራፋ ግንባታ ለማከናወን እቅድ እንዳላቸው ገልጸው እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፤ ይሁን እንጂ የካይሮ ባለሥልጣናት እቅዱ ፍልስጤማውያንን ድንበር አቋርጠው ወደ ግብፅ እንዲገቡ ለማስገደድ የሚወሰድ ርምጃ ነው የሚል ምላሽ መስጠታቸውን ጠቅሷል፡፡
ይህ የተሰማው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሰኔ 26/2017 በተካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 42ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ “ሕዳሴ ግድብ አልቋል” ብለው ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው፡፡ በስብሰባው ላይ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ የምርቃት ሥነ ሥርዐት ላይ ግብጽ እና ሱዳን እንዲሳተፉ ግብዣ ማቅረባቸውም ይታወሳል፡፡ “ሕዳሴ ግድብ አልቋል” ሲሉ በይፋ የተናገሩት ዐቢይ፤ “ከመመረቁ በፊት ብንረብሽ ብለው የሚያስቡ ሰዎች አሉ፤ ግን እናስመረቀዋለን” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
በዚሁ ንግግር ላይ ለታችኛው ተፋሰስ ሀገሮች ባስተላለፉት መልዕክት፤ ግድቡ ለግብፅና ለሱዳን በረከት መሆኑን በመግለጽ፤ የሚመጣው ልማትና ኢነርጂ ለሁሉም ሀገራት የሚተርፍ ከመሆኑ ባሻገር የግብጹን አስዋን ግድብ “አንድ ሊትር ውሃ አለመቀነሱን”ም አስረድተዋል፡፡ አያይዘውም ኢትዮጵያ ከታችኛው ተፋሰስ ሀገሮች ጋር “ለመነጋገር፤ ለመደራደር እና ለመሥራት” አሁንም ዝግጁ መሆኗን በድጋሚ አረጋግጠዋል፡፡
ለግብጽ ያቀረበችው ሐሳብ ውድቅ ተደርጎባታል የተባለችው አሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ከአንድ ሣምንት በፊት ሐምሌ 7/2017 ከሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ዋና ጸሐፊ ማርክ ሩቴ ጋር በዋይት ሐውስ ባደረጉት ውይይት የሕዳሴ ግድብን ጉዳይ አንስተዋል፡፡ ለግብፅ ወገንተኝነታቸውን በግልጽ ባንጸባረቀ መልኩ ባደረጉት በዚህ ንግግር፤ “የሕዳሴ ግድብ ወደ ናይል የሚሄደውን ውሃ የሚዘጋ ነው” ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ በዚሁ ጉዳይ ላይ “መፍትሔ ለማምጣት እየሠሩ” መሆኑን የጠቆሙት ትራምፕ፤ ጉዳዩ መፍትሔ እንደሚያገኝ ከመግለጽ ባሻገር የሰጡት ምብራሪያ የለም፡፡ አክለውም ሀገራቸው ለግድቡ ግንባታ ገንዘብ ድጋፍ ማድረጓንም ተናግረዋል፡፡ ይህን የትራምፕን ንግግር የግብጽ ፕሬዝዳንት ዓብዱልፈታህ አል ሲሲ አድንቀውታል፡፡
ለፕሬዝዳንቱ ንግግር ምላሽ የሰጠው በእስራኤል የኢትዮጵያ ኤምባሲ፤ የግድቡ ግንባታ የተከናወነው በአሜሪካም ሆነ በየትኛውም የውጭ የገንዘብ ድጋፍ ሳይሆን በኢትዮጵያውያን መዋጮ መሆኑን በመግለጽ፤ በግድቡ ዙርያ የተሳሳተ አስተያየት መስጠት “ቀጣናዊ መተማመንን ስለሚሸረሽር” የውጭ አካላት “በእውነት ላይ የተመሠረተ መረጃ ብቻ” እንዲሰጡ አሳስቧል፡፡
የጋዛ ነዋሪዎችን የማፈናቀል እቅድ ያላት እስራኤል ሞሳድ በመባል በሚጠራው የስለላ ድርጅት ዳይሬክተር ዴቪድ ባርኔያ አማካኝነት ባለፈው ሣምንት ለአሜሪካ ባለሥልጣናት በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያንን ከጋዛ እንዲወስዱላቸው ለኢትዮጵያ፣ ኢንዶኔዥያ እና ሊቢያ ማበረታቻ በመስጠት እንዲያሳምኑላቸው ጥያቄ ማቅረባቸው አክሲዮስ የተባለው የዜና ድረ ገጽ ባለፈው ሣምንት መጨረሻ አስነብቧል፡፡
ባርኔያ ለአሜሪካ ባለሥልጣናት ኢትዮጵያን ጨምሮ ሦስቱ ሀገሮች በርካታ ቁጥር ያላቸውን ፍልስጤማውያን ከጋዛ ለመቀበል “ክፍት” መሆናቸውን ገልጸዋል ቢባልም፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ማብራሪያ አልሰጠም፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












