Homeዜናና ወቅታዊዜናእንግሊዝ እና ፈረንሳይን ጨምሮ 25 ሀገሮች በጋዛ ላይ የሚሰነዘረው ጥቃት በአፋጣኝ እንዲቆም...

እንግሊዝ እና ፈረንሳይን ጨምሮ 25 ሀገሮች በጋዛ ላይ የሚሰነዘረው ጥቃት በአፋጣኝ እንዲቆም ጥሪ አቀረቡ

ፈረንሳይን እና እንግሊዝን ጨምሮ 25 ሀገሮችን ያካተተ ቡድን እስራኤል በጋዛ ላይ ለ21 ወራት የቀጠለችውን ጦርነት እንድታቆም ባወጡት የጋራ መግለጫ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ቡድኑ ፍልስጤማውያን ላይ የሚደርሰው ስቃይ በመጠን “ከፍተኛ ደረጃ ላይ” መድረሱን ገልጿል፡፡

በጋራ መግለጫው ላይ ሁሉም አካላት እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህን አስከፊ ጥቃት “በአስቸኳይ፣ ያለ ቅድመ ሁኔታ እና በዘላቂነት” ማስቆም እንዲችሉ የጋራ ጥረት እንዲደረግ አሳስቧል፡፡ ይህን ለማሳካት አሜሪካ፣ ኳታር እና ግብፅ ለሚያደርጉት ጥረት ሙሉ ድጋፍ አለን ብለዋል፡፡

የጋዛ ጥቃት እንዲቆም የሚጠይቀው የሀገሮቹ ጥሪ የመጣው፤ እስራኤል በማዕከላዊ ጋዛ ከሚገኙት የመጨረሻዎቹ የሕፃናት ማሳደጊያዎች መካከል አንዱን በቦምብ ባወደመችበት እለት ነው። ሚልድ ኢስት ዐይ እንደዘገበው፤ ጥቃት የተሰነዘረባቸው ሕፃናት ቦርሳቸውን በጀርባቸው እንደያዙ በደም ጨቅይተው መምሕራን እና መንገደኞችን እገዛ ሲጠይቁ ታይተዋል፡፡

ከቅርብ ቀናት ወዲህ በጋዛ ያለው ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን የጠቆመው ዘገባው፤ ባለፈው እሑድ የዓለም የምግብ ፕሮግራም “የጋዛ የረሐብ ቀውስ አስከፊ ደረጃ ላይ ደርሷል” የሚል መግለጫ ማውጣቱንም አስታውሷል፡፡

በዓለም የምግብ ፕሮግራም መረጃ መሠረት፤ ንጹሐን በሰብዓዊ ርዳታ እጥረት ምክንያት እየሞቱ ነው፡፡ በጨመረው የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሳቢያ 90 ሺሕ ሴቶችና ልጆች አስቸኳይ ሕክምና ያስፈልጋቸዋል። ከሦስት ሰዎች አንዱ ደግሞ ለቀናት ምግብ ሳይመገብ ይቆያል፡፡

የጋዛ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ይህን በመደገፍ ባወጣው መረጃ፤ ቢያንስ 19 ፍልስጤማውያን እሑድ እለት በረሐብ እንደሞቱና በመቶዎች የሚቆጠሩ ደግሞ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምክንያት የመሞት አደጋ ተጋርጦባቸዋል ብሏል፡፡

ከጀርመን በስተቀር በርካታ የአውሮፓ ኅብረት ሀገሮችን ያካተተው ቡድን፤ “አስቸኳይ የተኩስ አቁምን ለመደገፍ ተጨማሪ ርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆናቸውን” ገልጸዋል፡፡ መግለጫው በተጨማሪም በእስራኤል የሚደገፈውን የጋዛ የሰብአዊነት ፋውንዴሽንን “አደገኛ” ብሎ በመፈረጅ ለፍልስጤማውያን “የሰውነት ክብር” የነፈገ ድርጅት ነው ብሎታል፡፡

አክሎም “በጋዛ የርዳታ አቅርቦቱ በመጠን በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ መምጣቱን በመጥቀስ፤ ሕፃናትን ጨምሮ መሠረታዊ የሆኑ የንጹሕ መጠጥ ውሃ እና የምግብ ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት በሚያደርጉት ጥረት ሰላማዊ ዜጎችን በሰብዓዊነት የጎደለው መንገድ መገደላቸውን አውግዟል፡፡ የእስራኤል መንግሥት ለሲቪል ሕዝብ አስፈላጊ የሆነ የሰብዓዊ ርዳታ አለመስጠቱ ተቀባይነት እንደሌለው የገለጸ ሲሆን፣ እስራኤል “በዓለም አቀፍ የሰብአዊ ሕግ መሠረት ያለባትን ግዴታ እንድትወጣም” አሳስቧል።

እስራኤል ከመስከረም 26/2016 አንስቶ በጋዛ ያለማቋረጥ በምትሰነዝረው የቦምብ ጥቃት የከተማውን ሕዝብ ከማፈናቀል ባሻገር ከ58 ሺሕ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular