የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የ2017 ምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ፤ ሐምሌ 13/2017 የመራጭነት ምዝገባ መጠናቀቁን ካሳወቀ በኋላ በድጋሚ በሁለት ክልሎች አንድ ሣምንት የመመዝገቢያ ጊዜ ፈቅዷል።
ቦርዱ ዛሬ ማክሰኞ ሐምሌ 15/2017 ምሽት ባወጣው መግለጫ እንዳሳወቀው፣ ምዝገባው የተራዘመው በአማራ እና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ነው።
በክልሎቹ የመጅሊስ ምርጫ ምዝገባ ሂደቱን ከነገ ረቡዕ ሐምሌ 16 እስከ ረቡዕ ሐምሌ 23/2017 ለማስቀጠል የወሰነው በሦስት ምክንያቶች መሆኑን ገልጿል። እነዚህ ምክንያቶች በክልሉ በነበረው የምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ አለመግባባት ምዝገባ የተቋረጠ መሆኑ፣ የቁሳቁስ ሥርጭት በጊዜ ባለመዳረሱ እና በዚህ ሳቢያ የሥልጠናና የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ በወቅቱ አለመሰጠቱ ናቸው።
ችግሮቹ እንደተፈቱ የጠቆመው ቦርዱ፣ ከነገ ጧት 12 ሰዓት ጀምሮ የማኑዋል እና የኦንላይን የምዝገባ ስልቶች እንዲቀጥል ውሳኔ ማሳለፉን አስታውቋል። በዚህም ምዝገባውን ያልጀመሩ አካባቢዎች እንዲጀምሩ እና ምዝገባውን ጀምረው በተለያየ ምክንያት ያቋረጡ አካባቢዎች ይቀጥላሉ ብሏል።
የምርጫ አስፈጻሚ ቦርዱ የምርጫውን መጠናቀቅ ባሳወቀበት ቀዳሚ መግለጫ፣ ለአንድ ወር በቆየው ሒደት የተመዘገበውን የመራጮች ቁጥር ይፋ አላደረገም። (ሚንበር ቲቪ)












