አሜሪካ ፍልስጤምን በአባል ሀገርነት በመቀላቀሉ ምክንያት፤ ከተባበሩት መንግሥታት የትምሕርት፣ የሣይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) ልትወጣ መሆኑን የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አስታወቀ፡፡ መሥሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ፤ የአካታችነት ችግር አለበት ባለው ድርጅት ላይ “ፀረ እስራኤል ንግግር እንዲዛመት አስተዋጽኦ ያበረከተ ነው” የሚል ውንጀላ አቅርቧል፡፡
በውሳኔው መሠረት አሜሪካ ከድርጅቱ አባልነት የምትለቀው እ.አ.አ በዲሴምበር 31/2026 ይሆናል፡፡
ሚድል ኢስት ዐይ እንደዘገበው፤ ሀገሪቱ ከዚህ ቀደም በዩኔስኮ ላይ ቅሬታ ያሳደረችው በ2011 የድርጅቱ አባላት ፍልስጤም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሙሉ አባል እንድትሆን ያሳለፉትን ውሳኔ ተከትሎ ነው፡፡ ዋሽንግተን የተባበሩት መንግሥታት አካላት ፍልስጤምን እንደ ሀገር ዕውቅና ለመስጠት የሚወስዱትን ማንኛውንም ርምጃ እንደምትቃወም አስታውሷል፡፡
ውሳኔውን በተመለከተ የተናገሩት የስቴት ዲፓርትመንት ቃል አቀባይ ታሚ ብሩስ፤ “የዩኔስኮ ‘የፍልስጤም ግዛት’ን እንደ አባል ሀገር የመቀበል ውሳኔ የአሜሪካን ፖሊሲ የሚፃረር እና በድርጅቱ ውስጥ ለፀረ እስራኤል ንግግሮች መስፋፋት አስተዋፅኦ ያበረከተ፤ በጣም ችግር ያለበት ነው” ብለዋል። አክለውም “ዩኔስኮ ከፋፋይ ማኅበራዊና ባሕላዊ ጉዳዮችን ለማራመድ ይሠራል” ሲሉ ከሰዋል፡፡ ቃል አቀባዩዋ ለዚህ በምክንያት የጠቀሱት ከአሜሪካ የመጀመሪያ የውጭ ፖሊሲ ጋር የሚጋጭ ርዕዮተ ዓለም ነው ያሉትን የተባበሩት መንግሥታት ዘላቂ የልማት ግቦች ላይ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን ነው፡፡
ኒውዮርክ ፖስት እንደዘገበው ከሆነ ደግሞ፤ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በየካቲት ወር የሀገሪቱን አባልነት እንዲገመገም ትዕዛዝ ሰጥተው ነበር፡፡ ግምገማው በድርጅቱ ውስጥ አለ ያሉት “ፀረ ሴማዊነት ወይም ፀረ እስራኤል ስሜት” ላይ ያተኮረ ነበር። በፕሬዝዳንቱ አስተዳደር ውስጥ ያሉ ባለሥልጣናት ዩኔስኮ “ለፍልስጤምና ለቻይና ድጋፍ የሚሠጥ እንዲሁም በልዩነት፣ በፍትሐዊነት እና በአካታችነት ፖሊሲዎች ላይ ከመጠን በላይ የሚጨነቅ ነው” የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል፡፡
የእስራኤሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዴዎን ሳር፤ ስቴት ዲፓርትመንት የሰጠውን መግለጫ በደስታ ተቀብለነዋል ሲሉ፤ የዩኔስኮ ኃላፊ ኦድሬ አዙሌይ በበኩላቸው የቀረበውን ውንጀላ “የዩኔስኮን ጥረት፤ በተለይም በሆሎኮስት ትምህርት እና ፀረ ሴማዊነትን በመዋጋት ረገድ መሬት ላይ ያለውን እውነታ የሚቃረን ነው” ብለዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ከአሜሪካ ስምንት በመቶ ገደማ በጀት የሚያገኘው ዩኔስኮ፤ ርምጃው ሊከተል ይችላል በሚል ግምት ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን በመግለጽ፤ የገንዘብ ምንጮቹንም በማስፋት ላይ እንደሚገኝ አዙሌይ ተናግረዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በተመሣሣይ በ2017 በመጀመርያ የሥልጣን ዘመን ሀገራቸውን ከዩኔስኮ አባልነት አስወጥተው የነበረ ቢሆንም ተከትሎ የመጣው የባይደን አስተዳደር ወደ ሥልጣን ሲወጣ ውሳኔውን ቀልብሶታል። ባይደን በ2023 ሀገራቸውን ወደ ድርጅቱ ሲመልሱ “የቻይናን ተጽዕኖ” ለመቋቋም እንደገና መቀላቀል በጣም አስፈላጊ መሆኑን አስተዳደራቸው ገልጿል፡፡
መቀመጫውን ፓሪስ ያደረገው ዩኔስኮ የተቋቋመው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጠናቀቅ በኋላ በ1945 ነው። ከመሥራች ሀገሮች መካከል አሜሪካ አንደኛዋ ነች፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












