Homeዜናና ወቅታዊዜናየተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በጋዛ ጉዳይ ርምጃ እንዲወስድ የእስላማዊ ትብብር ድርጅት...

የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በጋዛ ጉዳይ ርምጃ እንዲወስድ የእስላማዊ ትብብር ድርጅት አሳሰበ

የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በወቅቱ ወኪል ቱርክ አማካኝነት፤ በጋዛ ጉዳይ ርምጃ እንዲወስድ የእስላማዊ ትብብር ድርጅት አሳስቧል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቱርክ ቋሚ ልዑክ አሕመድ ይልድዝ፤ ይህን ማሳሰቢያውን የሰጡት በመካከለኛው ምሥራቅ ሁኔታ ላይ በተደረገው የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ወቅት ነው፡፡

በቅርብ ጊዜ በጋዛ ውስጥ ዘላቂ የተኩስ አቁም ላይ የተደረጉ ድርድሮች የፈነጠቁት ተስፋ አፋጣኝ መፍትሔ አለማምጣቱን “አሳዛኝ” ሲሉ የገለጹት ቋሚ ልዑኩ፤ በዚህ ምክንያት የፍልስጤም ሕዝብ በተለይም በጋዛ ውስጥ “በቀጠለው ሕገ ወጥ ወረራ” ምክንያት “ተከታታይነት ያለው አሰቃቂ ፈተና እንዲጋፈጥ” መገደዱን ተናግረዋል፡፡

በጋዛ ያሉ ሰዎች ለሕይወት አስጊ የሆኑ ሁኔታዎችን እየተጋፈጡ በመቀጠላቸው በየቀኑ የበርካታ ንጹሐን ሕይወት እየተቀጠፈ ነው በማለትም የሁኔታውን አስከፊነት አስረድተዋል፡፡

ይልድዝ እስላማዊ ትብብር ድርጅትን በመወከል በእስራኤል ጦር በጋዛ ከተማ እየተፈጸመው የሚገኘውን “የዘር ፍጅት ወንጀል እና በግዳጅ ማፈናቀል” በማውገዝ፤ ድርጅቱ እነዚህን ድርጊቶች “የጦር እና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች” በሚል መፈረጁን ገልጸዋል፡፡

በዚህ ውይይት ላይ ሌላው ያነሱት ጉዳይ ፍልስጤማውያንን ለማፈናቀል በእስራኤል ባለሥልጣናት የሚደረገውን እንቅስቃሴ የተመለከተ ነው፡፡ “የጋዛ ተወላጅ ፍልስጤማውያንን በኃይል ለማስፈናቀል የሚደረገው ይህ አካሄድ መሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶችን እንዲሁም ሁሉንም የዓለም አቀፍ ሕጎች እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚወክል ነው” ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪም “ለዘመናት በዘለቀው የመካከለኛው ምሥራቅ ቀውስ ታሪክ ውስጥ በጣም ወሳኝ በሆነው በዚህ ወቅት ዓለም አቀፍ ሰላም እና ደኅንነት እንዲጠበቅ ዋነኛ ኃላፊነቱን እንዲወስድ” ምክር ቤቱን መጠየቁን አናዶሉ ኤጀንሲ ዘግቧል፡፡

የእስላማዊ ትብብር ድርጅት ካቀፋቸው 57 አባል ሀገሮች መካከል 48ቱ ሙስሊሞች ናቸው። ድርጅቱ “የሙስሊሙ ዓለም የጋራ ድምጽ” እንደሆነና “የሙስሊሙ ዓለም ጥቅሞችን በዓለም አቀፍ ሰላም እና ስምምነት መንፈሥ ለመጠበቅ እንደሚሠራ” ይገልጻል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በአውሮፓ ኅብረት ቋሚ ልዑካን አሉት። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular