Homeዜናና ወቅታዊዜናፈረንሣይ በመስከረም ወር በሚካሄደው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለፍልስጤም ሀገረ መንግሥት ዕውቅና...

ፈረንሣይ በመስከረም ወር በሚካሄደው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለፍልስጤም ሀገረ መንግሥት ዕውቅና እንደምትሰጥ ይፋ አደረገች

የፈረንሣይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፤ ሀገራቸው በመስከረም ወር በሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (የተመድ) ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለፍልስጤም ሀገረ መንግሥት ዕውቅና እንደምትሰጥ አሳውቀዋል፡፡ ውሳኔውን አሜሪካ በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ ማርኮ ሮቢዮ በኩል ተቃውመውታል፡፡

ፕሬዝዳንት ማክሮን ይህን ያስታወቁት በኤክስ ገጽ ባሠፈሩት ጽሑፍ ነው፡፡ “ፈረንሳይ ለፍልስጤም ሀገረ መንግሥት ዕውቅና እንድትሰጥ ውሳኔ አሳልፌያለሁ” ያሉት ማክሮን፤ “በመስከረም ወር በሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ይህን ሐሳብ ይፋ አደርጋለሁ” ሲሉ አሥፍረዋል፡፡

በዚሁ ጽሑፍ ላይ በአሁኑ ሰዓት በጋዛ አንገብጋቢው ጉዳይ ጦርነቱን በማቆም “ለንጹሐን እፎይታ መስጠት ነው” ብለዋል፡፡

ማክሮን ለፍልስጤም ሀገረ መንግሥት ዕውቅና ለመስጠት አስቀድመው ዕቅድ ያስቀመጡት፤ ባለፈው ወር ሳይካሄድ በቀረው የተባበሩት መንግሥታት ጉባዔ ላይ ነበር፡፡ ጉባዔው ሳይካሄድ የቀረው እስራኤል በኢራን የኑክሌር ጣቢያዎች ላይ ጥቃት መሰንዘሯን ተከትሎ ነው፡፡  

ከማክሮንን ውሳኔ ይፋ መደረግ በኋላ እስራኤል እና አሜሪካ ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡ የእስራኤል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የፍትሕ ሚኒስትር ያሪቭ ሌቪን፤ ፈረንሣይ ለፍልስጤም ዕውቅና ለመስጠት የወሰደችውን ርምጃ “በፈረንሳይ ታሪክ ላይ ጥቁር ጠባሳ ያሳረፈና ለሽብርተኝነት ቀጥተኛ ድጋፍ [የሚሰጥ] ነው” በማለት አውግዘውታል።

በተመሣሣይ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ፤ ሐሙስ ምሽት በኤክስ ላይ ባሠፈሩት ምላሽ፣ የማክሮን ውሳኔ “አስተዋይነት የጎደለው ነው” ሲሉ ተቃውመዋል፡፡ “ለሐማስ ፕሮፓጋንዳ መጠቀሚያ እንደሚሆን” የተጀመረውን የሰላም ሒደት “ወደ ኋላ የሚመልስ ነው” በማለትም አጣጥውታል፡፡

አያይዘውም ማክሮን ሀገራቸው ለፍልስጤም ዕውቅና ትሰጥበታለች ባሉት በመስከረም ወር በሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባዔ ላይ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንደማይሳተፉ ገልጸዋል፡፡

ከ193 የተባበሩት መንግሥታት አባል ሀገሮች መካከል ቢያንስ 142 የሚሆኑት በአሁኑ ወቅት ለፍልስጤምን ሀገረ መንግሥት ዕውቅና ሰጥተዋል፡፡ አሜሪካን፣ እንግሊዝንና ጀርመንን ጨምሮ በድርጅቱ ውስጥ ተጽዕኗቸው የጎላ ሀገሮች እስካሁን ድረስ ይህን ለማድረግ ፍቃደኞች አለመሆናቸውን ሚድል ኢስት ዐይ ዘግቧል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular