Homeዜናና ወቅታዊዜናሰው ሠራሽ ረሐብ በጋዛ

ሰው ሠራሽ ረሐብ በጋዛ

ሐሰን በርባኽ ፍልስጤማዊ ነው፤ እድሜው ደግሞ ሁለት ብቻ፡፡ እንደ አለመታደል ሆነና በዚህ እድሜው እንደ እኩዮቹ ማግኘት የነበረበትን የተመጣጠነ ምግብ በሰው ሰራሽ ምክንያት ማግኘት ሳይችል ቀረ፡፡ ረዘም ላሉ ወራት በቆየው በዚሁ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እና መጠማት ሳቢያ፤ ጉበቱ ላይ የጤና እክል ገጥሞት ሰውነቱ ተመርዞ ከአንድ ወር በፊት ሰኔ 17/2017 ከዱንያ ሕይወት ተሸኘ፡፡ ለሕፃኑ ሐሰን ዓለም እርሱን መመገብ ችሎ ለአንድ ቀን እንኳን ማደር ቢችል ኖሮ፤ ሦስተኛ ዓመቱን የሚደፍነው ከኅልፈቱ ማግሥት ነበር፡፡ ነገር ግን አልሆነም፡፡

ለሕፃኑ ኅልፈት ምክንያት የሆነው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በዘር ማጥፋት የተፈረጀው እስራኤል በጋዛ ላይ የምትሠነዝረው ጥቃት ነው፡፡ የእስራኤል ባለሥልጣናት ጥቃት መሰንዘራቸው ሳይበቃ፤ ወደ ጋዛ ከተማ የርዳታ አቅርቦት እንዳይገባ ክልከላ ከጣሉ አምስት ወራት አለፉ፡፡

ሐሰንን በሞት የተነጠቀችው እናት አማና፤ ስለ ልጇ ኅልፈት ስትናገር፡- “የሐሰን ጤንነት ማሽቆልቆል የጀመረው በመጋቢት ወር ነበር፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ በድንገት የሰውነት ክብደቱ ሁለት ኪሎ ቀነሰ፤ ሊቆም አልቻለም፤ ከቀን ወደ ቀን የክብደት መቀነሱ ቀጠለና ድምጹ ሰለለ” ብላለች፡፡ እናትየው ይህ ለነገረቻቸው ዲፌንስ ፎር ችልድረን ኢንተርናሽናል ፓለንስታይን የጥናት ቡድን አባላት፤ እነዚህ ነገሮች በፍጥነት ሲደራረቡ ልጄ በዝግታ እየተሰናበተኝ መሆኑን ጠረጠርኩ ያለችው በአቅመ ቢስነት ስሜት ውስጥ ነው፡፡

ሀሰን ከኅልፈቱ አስቀድሞ በሚያዝያ ወር አጋማሽ፤ በኻን ዩኒስ ወደሚገኘው ናስር ሆስፒታል ቢወሰድም፤ የሆስፒታሉ ሐኪሞች አንዳች ሊፈይዱለት አልቻሉም፡፡ ምክንያቱም በጋዛ ውስጥ እንደቀሩት ሌሎች የሕክምና ተቋማት ሁሉ በከፍተኛ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት የተጎዱ ሕፃናትን በአግባቡ ለማከም መድኃኒት፣ የሕክምና መሣሪያ፣ ኤሌክትሪክ፣ ምግብም ሆነ ንጹሕ የመጠጥ ውሃ አልተገኘም፡፡

ይህ የሰቆቃ ታሪክ የሕፃኑ ሐሰን እና እናት አሚና ብቻ አይደለም፡፡ በጋዛ ባለፉት ሣምንታት የሚወጡ መረጃዎች ሁሉ ይህንኑ ጠቋሚ ናቸው፡፡

የጋዛ ሕጻናትን ሰቆቃ መረጃ የሚያሰባስበው ዲፌንስ ፎር ችልድረን ኢንተርናሽናል ፓለንስታይን ባልደረባዋ ሚራንዳ ክሌላንድ፤ ከሁለት ቀን በፊት በሚድል ኢስት ዐይ ባስነበቡት ዘለግ ያለ ጽሑፍ ያረጋገጡትም ተመሣሣዩን ነው፡፡  

በከተማዋ ያሉ ፍልስጤማውያን በከፍተኛ ፍጥነት በረሐብ እየረገፉ መሆኑን ለዓለም ደጋግመው ለማስታወስ የሚሞክሩት ሚራንዳ፤ የጋዛ የጤና ባለሥልጣናት ባወጡት መረጃ እሑድ ዕለት ብቻ ቢያንስ 19 ሰዎች በረሐብ ሕይወታቸው ማለፉን አረጋግጠዋል ብለዋል፡፡ እስራኤል የሰብዓዊ ርዳታ እንዳይገባ የጣለችውን ክልከላ ስትቀጥል፣ ወታደራዊ ኃይሎቿም በራሷ በእስራኤል እና አሜሪካ ከጀርባ ከሚዘወረው ከጋዛ ሰብዓዊ ፋውንዴሽን ርዳታ የሚፈልጉ ፍልስጤማውያንን መግደላቸውንም ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን በየዕለቱ መዘገባቸው እንደቀጠለ ነው፡፡

በርግጥ አሁን የጋዛ ረሐብ ዜናውን ለዓለም የሚያሠራጩ ዓለም አቀፍ የዜና አውታር ባልደረቦችንም ደጅ አንኳኩቷል፡፡ ትናንት ሐሙስ ከጋዛ በሚያሠራጩት ዘገባ ላይ የገለልተኝኘት ጥያቄ የሚነሳበትን የእግሊዙን ቢቢሲን ጨምሮ ሬውተርስ፣ አሶሽየትድ ፕረስ እና አዣንስ ፍራንስ ፕረስ በጋዛ የሚገኙ “ባልደረቦቻችን ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን መመገብ እየተሳናቸው መምጣቱ እንዳሳሰበን ዓለም ይወቅልን ብለዋል፡፡ የዜና አውታሮቹ ይህን የገለጹበትን መግለጫ ለዓለም ሲያሠራጩ በጋዛ መሬት ላይ “የዓለም ዓይንና ጆሮ ሆነው ቆይተዋል” ያሏቸውን ጋዜጠኞች የእስራኤል ባለሥልጣናት የይለፍ ፍቃድ እንዲሰጣቸው በመጠየቅ ነው፡፡ መገናኛ ብዙኃኑ ባልደረቦቻችን እሕል ቀምሰው እንዲያድሩ መግባትና መውጣት ፍቀዱላቸው ብለዋል፡፡

መግለጫውን ያወጡት ምዕራባዊያን መገናኛ ብዙኃን ብቻ አይደሉም፡፡ በተመሣሣይ ረቡዕ እለት በጋዛ የሚፈጸመውን በተከታታይ በማጋለጥ የሚታወቀው የኳታሩ አልጀዚራ ሚዲያ ኔትወርክ፤ በከተማዋ የሚገኙ ጋዜጠኞቹ እና የመገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎች ለረሐብ በመጋለጣቸው፤ የመገናኛ ብዙኃን ማኅበረሰብ፣ የፕሬስ ነፃነት ድርጅቶች እና የሚመለከታቸው የሕግ አካላት ርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ለዚህ ጥሪ የእስራኤል ባለሥልጣናት እስካሁን ድረስ ምላሽ ለመስጠት የፈቀዱ አይመስልም፡፡ በጋዛ ሕፃናትን ጨምሮ የሁሉንም ሰው ሕይወት ሊቀጥፍ የሚችለው ይህ ረሐብ፤ ሰው ሠራሽ መሆኑን የሚገልጹት የዲፌንስ ፎር ችልድረን ኢንተርናሽናል ፓለንስታይን ባልደረባዋ ሚራንዳ ክሌላንድ፤ ሳይዛመት ሊገታ ይችል እንደነበረም ይከራከራሉ፡፡ ረሐብን ሙሉ በሙሉ ሊከላከሉት የሚቻል ጉዳይ መሆኑን የሚገልጹት ሚራንዳ፤ ሆን ተብሎ ካልተፈጸመ በስተቀር አንድ ልጅ እንኳ በረሐብ መሞቱ በአጋጣሚ ሊከሰት የሚችል አይደለም ይላሉ፡፡ ለዚህ በምክንያት የሚያቀርቡት ባለፈው ዓመት ጥር ወር ገደማ በጋዛ የመጀመሪያው ሕፃን በረሐብ ሕይወት ሲያልፍ፤ ቡድናቸው ለሚመለከታቸው አካላት ሪፖርት ቢያደርግም ሰሚ አለመገኘቱን ነው፡፡

በጽሑፋቸው ደጋግመው ረሐብ በአጋጣሚ የሚከሰት ነገር ሳይሆን ሰው ሠራሽ ነው የሚሉት ባለሞያዋ፤ ለዚህ ሁሉ የመጀመሪያዎቹ ተጠያቂዎቹ፤ ጥቃት በመፈፀም እና መሠረታዊ አቅርቦት ለተቸገሩ ፍልስጤማውያን እንዳይደርስ የሚያግድ ፖሊሲ የሚያራምዱት የእስራኤል ባለሥልጣናት ናቸው ብለዋል፡፡ የእስራኤል ደጋፊዎች ይህንን ቢያስተባብሉም፤ ባለስልጣናቱ ግን የዘር ማጥፋት ወንጀሉ በጀመረባቸው የመጀመርያዎቹ ቀናት ዓላማቸውን በግልጽ መናገራቸውንም ያስታውሳሉ፡፡

ለዚህ አስረጂ በሚል የሚጠቅሱት መስከረም 16/2016 የወቅቱ የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት ዮቭ ጋላንት “የጋዛን ቀጠና ሙሉ በሙሉ በከበባ ውስጥ እያስገባን ነው፤ ኤሌክትሪክ፣ ምግብ፣ ውሃና ነዳጅ ከዚህ በኋላ አይኖርም፤ ሁሉም ነገር ይቋረጣል፤ ማለታቸውን ማን ይዘነጋዋል” ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡

ሚራንዳ ደጋግመው በጋዛ ለሚፈጸመው ሁሉ ተጠያቂነቱ በእስራኤል ባለሥልጣናት ላይ ብቻ የሚወሰን አለመሆኑንም ይሞግታሉ፡፡ ሚራንዳ ይቀጥላላ፡-

“በአሁኑ ወቅት በጋዛ የሚኖሩ ሁሉም ሕፃናት በረሐብ እየረገፉ ነው። ለዚህ ስቃይ ተጠያቂው የእስራኤል ባለሥልጣናት ብቻ አይደሉም። የእስራኤል ባለሥልጣናት ፍልስጤማውያንን በረሐብ ለመቅጣት፣ በርካታ ሺሕ ኪሎ ግራም የሚመዝኑ ቦምቦችን በመኖሪያ ቤቶች፣ በትምህርት ቤቶች እና በሆስፒታሎች ላይ ሲያዘንቡ በዝምታ የተመለከቱ የዓለም መሪዎችም ተባባሪ ናቸው፡፡ ስለዚህ ተጠያቂ መሆን አለባቸው።

አሁንም ቢሆን ዝምታው ሊያበቃ ይገባል፡፡ ሦስተኛ ልደቱን ማክበር ሲኖርበት እናቱ በአቅመ ቢስነት እየተመለከተችው በረሐብ ላሸለበው ሕጻኑ ሐሰን ጊዜው ረፍዷል፡፡ ጡንቻቸው ዝሎ የውስጥ ሰውነት ክፍሎቻቸው በምግብና በውሃ እጦት ምክንያት ተዳክመው በከፍተኛ ሥቃይ ውስጥ በዝግታ ለሞቱት ለሌሎቹ ፍልስጤማውያን ሕፃናትም ጊዜው አልፏል።

አሁንም ግን በጋዛ የሚኖሩ አንድ ሚሊዮን የተራቡ ሕፃናት በቂ ምግብ የሚያገኙበትን ቀን በመጠባበቅ ላይ ናቸው። በጋዛ የሚፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል በአስቸኳይ እንዲቆምና የዓለም መሪዎች የፍልስጤም ሕፃናትንና ቤተሰቦችን ሕይወት ለማዳን፤ አስፈላጊውን ርምጃ እንዲወስዱ ጥሪ እናቀርባለን። በዚህ ጊዜ ከዚህ ያነሰ ነገር ማድረግ ፈጽሞ በቂ አይደለም።” (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular