የሳዑዲ ዐረቢያ የፀጥታ አካላት በቅድስቲቱ መካ ከተማ በካዕባ ውስጥ የፍልስጤምን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገ የታየውን ግብጻዊ ምዕመን በቁጥጥር ስር አውለውታል፡፡ የሀገሪቱ ባለሥልጣናት የወሰዱት ርምጃ ቅሬታ ማስነሳቱን ሚድል ኢስት ዐይ ዘግቧል፡፡
ምዕመኑ በካዕባ ውስጥ ድምጹን ጎላ በማድረግ “ዋ ኢስላማ!” ሲል ተደምጧል፡፡ ይህ አገላለጽ እስልምና እና ሙስሊሞች አደጋ ውስጥ በሚወድቁበት ጊዜ ጭንቀታቸውን ለመግለጽ የሚጠቀሙበት መሆኑን ያስታወሰው ዘገባው፤ ግለሰቡ የጋዛን የተራበ ሕዝብ ለመርዳት በአፋጣኝ ጣልቃ መግባት እንደሚያስፈልግ ተማጽኖ ያቀረበበት መሆኑንም አስፍሯል፡፡ ምዕመኑ አክሎም “ሙስሊሞች ሆይ! የጋዛ ሕፃናት እየሞቱ ነው” የሚል ጥሪ ድረሱላቸው የሚል ጥሪ አቅርቧል፡፡
ጥሪውን ካሰማ ከጥቂት ሴኮንዶች በኋላ በሥፍራው የነበሩ የፀጥታ አካላት በቁጥጥር ስር አውለውታል፡፡ ይህ ክስተት በኢስላም ቅዱስ ሥፍራዎች “ፖለቲካ ይዘት ያላቸውን መግለጫዎችን” በጥብቅ በምትከለክለው ሳዑዲ እንደገና ክርክር አስነስቷል። ባለሥልጣናት በሐጅ እና በዑምራ ወቅት የሀገሮችን ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ጨምሮ ሁሉንም መፈክሮች እና ምልክቶች እንደሚከለከሉ ከዚህ ቀደም ደጋግመው ይገልጻሉ፡፡ ይህን ርምጃ የሚወስዱት በቅዱሳኑ ሥፍራዎች የሚፈጸሙ ሃይማኖታዊ ተግባራት “ሰላም ለማስጠበቅ” መሆኑንም በምክንያትነት ያስቀምጣሉ፡፡
እ.አ.አ በ2023 አንድ እንግሊዛዊ ምዕመን የፍልስጤም መገለጫ የሆነውን ኪፋያ እና የፍልስጤምን መለያ ቀለም የያዘ መቁጠሪያ ይዞ በመገኘቱ በቁጥጥር ስር መዋሉን ዘገባው አስታውሷል፡፡ ከመካ ባሻገር የሀገሪቱ ባለስልጣናት እስራኤልን በሚተቹ ወይም በበይነ መረብ አማካኝነት ለጋዛ ያላቸውን ድጋፍ በሚገልጹ ዜጎች ላይ ርምጃ እንደሚወስዱም ይነገራል፡፡
የእስራኤል ጥቃት በጋዛ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት፤ በመካ የተደረገው የግብጻዊው የፍልስጤም ደጋፊ እስር፤ በሳዑዲ ዐረቢያ ለፍልስጤማውያን የሚደረግ ድጋፍ በወንጀል ፍረጃ ውስጥ ወድቋል የሚል ሥጋት ማሳደሩንም ዘገባው ጠቁሟል፡፡ (ሚንበር ቲቪ)












