Homeዜናና ወቅታዊዜናየፍልስጤም ሉዓላዊ ሀገርነት፣ የኒውዮርኩ የተመድ ጉባዔ እና አሜሪካ

የፍልስጤም ሉዓላዊ ሀገርነት፣ የኒውዮርኩ የተመድ ጉባዔ እና አሜሪካ

ፈረንሣይ እና ሳዑዲ ዐረቢያ ያስተባበሩት በፍልስጤም ጉዳይ ላይ የሚመክር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (የተመድ) ጉባዔ፤ ትናንት ሰኞ በኒውዮርክ ተጀምሯል፡፡ በዚህ ጉባዔ ላይ በዋነኝነት ፍልስጤምን ሉዓላዊ ሀገር ማድረግ የሁለትዮሽ መፍትሔ ለማምጣት ያስችላል የሚለው ሐሳብ ተደጋግሞ ተንጸባርቋል፡፡

አስቀድሞ በተያዘው የጊዜ ሠሌዳ መሠረት በሰኔ ሊካሄድ የታቀደው ጉባዔ የተራዘመው እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት በመሰንዘሯ ምክንያት ነው፡፡ ሀገሮች በውጭ ጉዳይ ሚኒትሮች በተወከሉበት ጉባዔ ላይ፤ እስራኤል እና አሜሪካ ተወካይ ሳይልኩ ቀርተዋል፡፡

ሚድል ኢስት ዐይ እንደዘገበው፤ አሜሪካ እና እስራኤል “በማኩረፍ” ከጉባዔው እንዲቀሩ ያደረገው አንደኛዋ አስተባባሪ ፈረንሣይ ለፍልስጤም የሉዓላዊ ሀገርነት ዕውቅና እሰጣለሁ ማለቷ ነው፡፡ ሀገሪቱ ይህን ይፋ ያደረገችው በፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኩል ነው፡፡

ማክሮን ለፍልስጤም በመጪው መስከረም ወር ዕውቅና እንደሚሰጡ ሲገልጹ፤ አሜሪካ አስቀድማ ተቃውሞ ያሰማችው በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊዋ ማርኮ ሩቢዮ አማካኝነት ነው፡፡ ሩቢዮ በኤክስ ገጽ ባሠፈሩት ጽሑፍ፤ ውሳኔውን “አስተዋይነት የጎደለው ነው” ሲሉ ነቀፌታ ሰንዝረዋል፡፡  

ሩቢዮ የሚመሩት መሥሪያ ቤት በይፋ ባወጣው መግለጫም፤ ውሳኔውን ብቻ ሳይሆን ከሰኞ አንስቶ ለሦስት ቀናት የሚዘልቀውን ጉባዔ “ፍሬ ቢስ” ነው ሲል አጣጥሎታል፡፡ ለሰላም የሚደረገውን ሒደት አስቸጋሪ የሚያደርግ እንደሆነም ገልጿል፡፡

አሜሪካ ጉባዔውን ብቻ ሳይሆን የፈረንሣይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ለፍልስጤም የሉዓላዊ ሀገርነት ዕውቅና እሰጣለሁ ማለታቸውንም “ዲፕሎማሲያዊ ጥረታችንን የሚያዳክም ነው” ስትል ተችታለች፡፡ ይሁን እንጂ ፈረንሣይ ከአሜሪካ ትችት ብታስተናግድም ዩናይትድ ኪንግደም ተመሣሣይ አቋም እንድታራምድ ለማግባባት ጥረት እያደረገች እንደምትገኝ ሚድል ኢስት ዐይ በዘገባው ጠቁሟል፡፡

በርግጥ ይህንኑ የፈረንሣይ ሐሳብ ከ200 በላይ የብሪታንያ የፓርላማ አባላት እንደደገፉት ባለፈው ጁመዓ ቢገልፁም፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ኬር ስታርመር ግን ተቃውመዋል የሚል መረጃ ወጥቷል። በዘገባው መሠረት የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ለፍልስጤም ዕውቅና እንዳይሰጥ በፈረንሣይ ላይ እንደሚደረገው ሁሉ ጫናውን የሚያሳርፈው የትራምፕ አስተዳደር ነው፡፡

ይህ በእንዲህ ባለበት እየተደረገ በሚገኘው የኒውዮርኩ የተመድ ጉባዔ ተሳታፊዎች፤ በፍልስጤም እና እስራኤል መካከል ሰላም ለማስፈን ከሁለት ሀገርነት መፍትሔ ውጪ “አማራጭ የለም” የሚል አቋም ማራመዳቸው ተገልጿል፡፡ ጉባዔውን ከሳዑዲ ዐረቢያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፈይሰል ቢን ፈርሐን ጋር ባንድነት የሚመሩት የፈረንሣይ አቻቸው ዣን ኖኤል ባሮ ይህንኑ ሐሳብ በድጋሚ አንጸባርቀዋል፡፡

አሜሪካ በተባበሩት መንግሥታት ጉባዔ ላይ ትችት ብትሰነዝርም፤ ፈረንሣይ እና ሳዑዲ ዐረቢያ ግን አሁንም ትራምፕ ወደ ውይይቱ እንዲመለሱ ለማድረግ ጥረት ማድረግ መቀጠላቸው ተሰምቷል፡፡ የሳዑዲ ዐረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፈይሰል ቢን ፈርሃንም “በጋዛ የሚሰነዘረውን ጥቃት በማስቆም የሁለት ሀገር መፍትሔ ሒደቱን ለማስጀመር” የትራምፕ ተሳትፎ “አስገዳጅ” ሊሆን ይችላል ብለዋል፡፡

በመስከረም ወር በሚካሄደው የተመድ ጉባዔ ላይ ቀድመው እንደማይሳተፉ የተገለጸው ፕሬዝዳንት ትራምፕ፤ የሳዑዲ ዐረቢያ እና እስራኤልን ግንኙነት ጤናማ ለማድረግ ተደጋጋሚ ሙከራ እንደሚደርጉ ይነገራል፡፡ የሳዑዲ ባለሥልጣናት ይህ እንዲሳካ እስራኤል የፍልስጤም ሉዓላዊ ሀገርነት እንዲረጋገጥ እንዲሁም በጋዛ ተኩስ አቁም ማድረግን እንደ ቅድመ ሁኔታ ያስቀምጣሉ፡፡

በዚህ መሃል በቀጠለው የሦስቱ ቀናት ስብሰባ፤ የፍልስጤም መንግሥት እውቅና ለማግኘት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ከማመቻቸት ባሻገር፣ የፍልስጤም አስተዳደር ማሻሻያ፣ የሐማስ ትጥቅ መፍታት እና የሁለት ሀገር መፍትሔ አካል በመሆን የዐረብ ሀገሮች ከእስራኤል ጋር ያላቸውን ግንኙነት መደበኛ ማድረግን ጨምሮ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ያተኩራል ተብሏል። (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular