Homeዜናና ወቅታዊሰሞነኛ ጉዳዮችለሐጅ የሚደረገው ‘ሌላኛው ፍልሚያ’

ለሐጅ የሚደረገው ‘ሌላኛው ፍልሚያ’

ሳዑዲ ዐረቢያ በዘንድሮው የሐጅ ሥነ ሥርዐት ክንውን ለመሳተፍ ከመላው ዓለም ሀገራት የተነሱ ምዕመናንን መቀበሏን እንደቀጠለች ነው፡፡ የሀገሪቱ ባለሥልጣናት ይፋ ያደረጓቸው መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ እስካሁን ድረስ ሳዑዲ ዐረቢያ የገቡ ምዕመናን ቁጥር አንድ ሚሊዮን ደርሷል፡፡ ከአንድ ሳምንት በታች ለቀረው የሐጅ ክንውን፣ በቀጣይ ቀናት ሌሎች አንድ ሚሊዮን ምዕመናን ወደ ሀገሪቱ ይዘልቃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ሳዑዲ ዐረቢያ እንግዶቹን የምታስተናግደው ለሥነ ሥርዐቱ ብቻ በሚል የተለየ ቪዛ አዘጋጅታ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የሐጅ ቪዛ ከያዙ ምዕመናን ውጪ ሌሎች እንግዶች ወደ ሀገሬ ቢገቡም ወደ ቅድስቲቱ መካ ከተማ እንዲዘልቁ አልፈቅድም በማለት የከተማዋን በሮች ቆልፋለች፡፡

ሀገሪቱ ከዚህ ቀደም እንዳስታወቀችው፣ የመካ በር ከተቆለፈ በኋላ ማንኛውም ምዕመን በየትኛውም ምክንያት በድንገት መካ ከተማ ውስጥ ያለ ሐጅ ቪዛ ቢገኝ ቅጣት ይጠብቀዋል፡፡ ሳዑዲ መቀጮ የሚያስከፍለውን ደንብ ያወጣችው በሥነ ሥርዐቱ ወቅት ሊከሰት የሚችለውን መጨናነቅ ለመቀነስ ነው፡፡ ሳዑዲ ዐረቢያ ይህን እርምጃ ይበልጥ ያጠናከረችው ከዘጠኝ ዓመታት በፊት ሚና ላይ አደጋ ከተከሰተ በኋላ ነው፡፡ ምዕመኑን ብቻ ሳይሆን የትራንስፖርት አገልግሎት የሰጡትንም ጭምር የሚያስቀጣውን ደንብ የጣሱ፣ በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር መዋላቸውን የሳዑዲ ዐረቢያ ጋዜጦች መዘገብ ጀምረዋል፡፡

ሳዑዲ ቁጥጥሩን ጠበቅ ብታደርግም፣ የመጣውን ለመቀበል የቆረጡ ከመላው ዓለም የተለያዩ ሀገራት ቀደም ብለው የተነሱ ምዕመናን የሐጅ ቪዛ በእጃቸው ሳያስገቡ መካ ውስጥ እንደሚገኙም ዘገባዎቹ ያመለክታሉ፡፡ እነዚህ ምዕመናን መካ ውስጥ የሚገኙት ሐጅ ሲጀመር ሥነ ሥርዐቱን ለመከወን ነው፡፡ ምዕመናኑ ይህን መንገድ የመረጡት በአብዛኛው ከገንዘብ ጋር በተገናኘ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ከእነዚህ ውስጥ የሆነው መገናኛ ብዙኃኑ የአባቱን ሥም ያልጠቀሱት ግብጻዊው ሙሐመድ፣ በአሁኑ ወቅት መካ ውስጥ በሚገኝ አፓርታማ ውስጥ በመቀመጥ የሐጅ ሥነ ሥርዐት እስኪጀመር ድረስ እየተጠባበቀ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ሙሐመድ ለምን ይህን እንዳደረገ ሲጠየቅ፣ ወጪ ቆጣቢ ሐጅ ለመፈጸም ነው ብሏል፡፡ የሙሐመድ ሀገር ግብጽ ለሐጅ ሥነ ሥርዐት 175 ሺሕ (የግብጽ) ፓዉንድ ታስከፍላለች፡፡ ሙሐመድ ከዚህ በተጨማሪም ሌላ ምክንያት ይጠቅሳል፤ ግብጽ በምከተለው የሐጅ አሠራር መሠረት ለአሥር ዓመት የሐጅ ዕድል ለማግኘት ዕጣ ይደርሰኛል ብሎ ቢጠባበቅም አልተሳለትም፡፡ ስለዚህ በቱሪስት ቪዛ መካ በመግባት ቀኑ እስኪደርስ ራሱን ከፀጥታ አካላት መሸሸግ መርጧል፡፡

ሳዑዲ ዐረቢያ በየዓመቱ የሐጅ ቪዛ ሰጥታ ከምታስተናግዳቸው እንግዶች ውጪ ቢያንስ 100 ሺሕ ምዕመናን ሳይፈቀድላቸው በሥነ ሥርዐቱ ላይ እንደሚታደሙ ትገልጻለች፡፡ (ሚንበር ቲቪ)

RELATED ARTICLES

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
ታላቅ ግብዣ

Most Popular